ደመናን በማበልጸግ ዝናብ ለማግኘት የሚያገለግል የኬሚካል መርጫ መሳሪያ በአገር ውስጥ መመረት ጀመረ

427

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1/2014 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ደመናን በማበልጸግ ዝናብ ለማግኘት ለሚካሄደው ቴክኖሎጂ የኬሚካል መርጫ መሳሪያ (ግራውንድ ጄነሬተር) በአገር ውስጥ መመረት ጀመረ፡፡

የደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂ በራሱ ደመና የሚፈጥር ሳይሆን በተከማቸ ደመና ተጨማሪ ዝናብ ማግኘት የሚያስችል ሳይንሳዊ ዘዴ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዚህ የቴክኖሎጂ ሂደት በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ለማዋል በተጀመረው የሙከራ ትግበራ ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ከመጡ ባለሙያዎች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመደረግ ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቲዎሮሎጂስት ተመራማሪ ለታ በቀለ እና በኢንፎርሜሸን መረብ ደህንነት አስተዳደር /ኢመደአ/ የሲስተም ኢንጂነሪንግ ኤክስፐርት እሸቱ አድማሱ ይህንኑ የቴክኖሎጂ ትግበራ በተመለከተ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂ በራሱ ደመና የሚፈጥር ሳይሆን ባለው ደመና ላይ ንጥረ ነገሮችን ወይንም ኬሚካሎችን በመጨመር ዝናብ የማግኘት የሳይንስ ጥበብ መሆኑን ያብራራሉ።

በዚህም ዝናብ ሰጪ ደመና ከተከማቸበት ቦታ በነፋስ እና በተለያዩ ነገሮች ሳይንቀሳቀስ ወይም ሳይበተን ተጨማሪ ዝናብ እንዲኖረው ይደረጋል።

የዝናቡን መጠን እንዲጨምር የሚያደርጉትን ኬሚካሎችም በአውሮፕላን፣ በድሮን፣ በሮኬት ወይም ግራውንድ ጄነሬተር በሚባሉ ቴክኖሎጂዎች ወደ ደመናው ማድረስ የሚቻል መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

የኢንፎርሜሸን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የሲስተም ኢንጂነሪንግ ኤክስፐርት እሸቱ አድማሱ እንደሚሉት፤ ቴክኖሎጂው ደመናን ዝናብ ሰጭ የማድረግ እድል የሚያሰፋ ነው።

በወቅት ላይ ተንጠልጥሎ የሚገኘውን የእርሻ ሥራ በማሻሻል የማምረት አጋጣሚን ለማስፋት ቴክኖሎጂው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቲዎሮሎጂ ተመራማሪው ለታ በቀለ፤ ከቴክኖሎጂው መጀመር በተጓዳኝ የእውቀት እና ክህሎት ልምድ እየተወሰደበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከቴክኖሎጂ ሽግግር በተጨማሪ ደመናን በማበልጸግ ዝናብ ለማግኘት ለሚደረገው ሂደት ለኬሚካል መርጫነት የሚያገለግለው ግራውንድ ጄነሬተር በኢንሳ መመረት መጀመሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት አንጻር ለደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂ 12 ራዳሮች እንደሚያስፈልጉ የጠቀሱት አቶ ለታ አሁን ላይ ሦስት ራዳሮች ወደ አገር ውስጥ በመግባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ደመናን በማበልጸግ ቴክኖሎጂ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ኢራን፣ ህንድ፣ ታይላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግድም እና ሌሎች አገራት ይጠቀሳሉ።

በዓለም ላይ ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂ የተጀመረው ከ76 ዓመታት በፊት ቢሆንም በኢትዮጵያ የተጀመረው ባለፈው ዓመት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም