በድሬዳዋ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ቤተሰቦች የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ ነው

80

ድሬዳዋ ፤ ሚያዝያ 1/2014(ኢዜአ) በድሬዳዋ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ቤተሰቦችና በማህበር የተደራጁ ወጣቶች የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን ተናገሩ።

በከተማዋ ሁሉም በየቤቱ የጓሮ አትክልት እንዲያለሙ የሚያበረታታበት የከተማ ግብርና ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል፡፡  

በከተማዋ በልማቱ ቀደም ብለው የተሰማሩ ቤተሰቦች ባላቸው አነስተኛ መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት  የቤተሰብ ፍጆታቸውን  መሸፈን መቻላቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በከተማው ''ጫፍ ጎሮ'' አካባቢ የሚኖሩት ወጣት አህመድ አብዱላሂ ከሶስት ጓደኞቹ ጋር እውቀት፣ ጉልበትና ከቤተሰብ የተሰጣቸውን ድጋፍ አቀናጅተው ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ቃሪያ፣ ጎመን ቲማቲም  በመትከል ጥሩ ምርት እያገኙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ባለፈው ዓመት ሙዝና ፓፓያ ለገበያ በማቅረብ ከ40 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን  ጠቅሷል፡፡

አሁን መንግስት ለከተማ ግብርና ትኩረት መስጠቱ ሰው ባለው ትንሽ መሬት ላይ ቢያንስ ለቤተሰቡ የሚሆን የጓሮ አትክልት እንዲያመርት ያበረታታል ብሏል፡፡

ወይዘሮ አሊያ አደም ደግሞ በትንሿ  መሬታቸው ላይ የተከሏቸው ሙዝና ፓፓያ ገቢ እያስገኙልኝ ነው ይላሉ፡፡

''አንድም ቀን አትክልት ከገበያ ገዝቼ አላውቅም፤ በቆፈርናት ጉድጓድ በምናገኘው ውሃ ታግዘን  የተከልናቸውን አትክልት እየተመገብን ነው፤ አስተዳደሩ እገዛ ካደረገልን ለገበያ ለማቅረብ እንችላለን'' ብለዋል፡፡

''የድሬዳዋ መሬት ለምና የከርሰ ምድር ውሃ ያለው በመሆኑ ጉልበቴና እውቀቴን ተጠቅሜ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት የቤተሰቤን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ችያለሁ'' ያሉት  አቶ  ጀማል ዩሱፍ የተባሉ አልሚ ናቸው፡፡

ለቤተሰባቸው የጓሮ አትክልት ከገበያ እንደማይገዙ  የተናገሩት አቶ ጀማል፤ መንግስት የጓሮ አትክልት ሥራ ሁሉም ቤተሰብ እንዲሞክረው ያስተላለፈው ጥሪ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።

ዘርፉ ድሬዳዋ ላይ በደንብ የሚሰራ ቤተሰብን ለመመገብ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግስት በከተማ ግብርና ለተሰማሩት ምርጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር፣ የጫጩትና የወተት ላም ዝርያዎችን ቢደግፍና በተመጣጣኝ ዋጋ ቢያቀርብ በራስ ጉልበትና ሃብት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

በከተማ ግብርና ለ45 ሰዎች የሥራ እድል  እንደፈጠሩ የሚናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሜሪ ማዘንጊያ ናቸው።

በዚህም የአትክልትና ፍራፍሬ፣ ወተትና፣ የወተት ተዋፅኦ እንዲሁም የእንቁላል ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱ ጥሩና ሁሉም ቤተሰብ ባለው ትንሽ መሬት የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬን እንዲተክል ያበረታታል ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች የስራቸው እንቅስቃሴ እንደተመለከቱላቸውና ይህም ለበለጠ ስራ እንዳነሳሳቸው አስታውቀዋል።

አስተዳደሩ ያለሙትን መሬት ህጋዊ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የካቢኔ አባላት  የከተማ ግብርና በድሬዳዋ በህዝብ ንቅናቄ በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን፣ በከተማው ውስጥ የተካሄዱ የሚገኙ የዘርፉ እንቅስቃሴ አበረታተዋል፡፡

ከንቲባው የከተማ ግብርና ለአየር ንብረት ለውጥና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ባለው ድርሻ ውጤታማ እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የመስኖና የቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ሰሞኑን በድሬዳዋ የአትክልትና ፍራፍሬ ሰርቶ ማሳያዎችና የምርምር ውጤቶችን በመመልከት በከተማ ግብርና መስክ ያላትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች የመጀመሪያዋ ከተማ ለመሆን እንድትተጋ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም