የጥናትና ምርምር ውጤቶች የማህበረሰብ ለውጥ እንዲያረጋገጡ በቅንጅት ሊተገበሩ እንደሚገባ ተመለከተ

522

ዲላ፤ መጋቢት 30/2014 (ኢዜአ) የጥናትና ምርምር ውጤቶች የማህበረሰብ ለውጥ እንዲያረጋግጡ ባለድርሻ አካላት ተገቢ ተሳትፎ በማድረግ በቅንጅት ሊተገበሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

“ምርምር ለሁለተናዊ ህብረተሰብ ለውጥ“ በሚል መሪ ሀሳብ 11ኛው ሀገር አቅፍ አውደ ጥናት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ   " የታዳሽ ኃይል ልማት በኢትዮጵያ እድሎች እና ተግዳሮቶች” በሚል ርዕሰ ንግግር ያደረጉት በኖሮዊ ላይፍ ኦፍ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሙይዋ ሳሙኤል አዳራሞላ፤ ኢትዮጵያ ከውሀ፤ ነፋስና ጂኦተርማል ታዳሽ ሃይል የማመንጨት ያልተነካ እምቅ አቅም አላት ብለዋል።

ይሁንና ሃብቱን በጥናት ያለመለየትና የፋይናንስ እጥረት ከተቋማት አቅም ማነስ ጋር ተዳምሮ ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል።

የፖሊስ አውጭዎችና መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር ሀብቱን ከመጠቀም ባለፈ በሃይል አቅርቦት እጥረት የሚቸገሩ  80 በመቶ የሀገሪቱን ዜጎች መድረስ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለይ በዘርፉ የሚወጡ የጥራትና ምርምር ውጤቶች የማህበረሰቡን ችግርን እንዲፈቱ ምሁራን፣ መንግስትና ኢንዱስትሪዎች በቅንጅት ሊተገብሩ እንደሚገባ  ተናግረዋል።   

ጠቃሚና ሕይወት አድን የሆኑ መድሃኒቶች በጥናት ግኝቶች ታግዘው ወደ ሀገር ውስጥ ባለመግባታቸው ለእጥረቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በህጻናት መድሃኒት አጠቃቀም ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት መምህር አንተነህ በላይ ናቸው።

በተለይ ሰፊውን የሀገሪቱን በጀት የሚሸፍነው የመድሃኒት ግዢ ህብረተሰቡ ሳይጠቀም የአገልግሎት ጊዜው የሚያበቃ በመሆኑ በህጻናት መድሃነት አወሳሰድ ላይ ጭምር ተፅዕኖ ማሳደሩን በጥናተ መረጋገጡን አብራርተዋል።

የምርምር ውጤቶችም ወደ ታች ወርደው የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንስቶ በየደረጃው የሚገኝ የመንግስትና አጋር አካላተ  የትብብር ስራችንን ማጠናከር አለብን ብለዋል።

በውሃና ኢነርጅ ሚኒስተር የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደበበ ደፈርሶ በበኩላቸው፤ ከ10 የሚልቁ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችንና እነሱን ማዕከል አርድገው የሚፈሱ ወንዞችን እንዲሁም ረግረጋማ ቦታዎችን ማልማት እውቀት እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

በተፋሰሱ የሚገኙ የውሃ ሃብቶች እንዲጠበቁና ለተሻለ ጥቅም እንዲውሉ በምርምርና ጥናት ከመደገፍ ባለፈ የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ አቅሞችን በማሰባሰብ የተፋሰስ ልማት እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ይህም የውሃ አጠቃቀምና ምድባን በመለየት የውሃ፣ ሃይልና ግብርና ጠቀሜታ ማረጋገጥ የሚችሉ አምስት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የምርምር ውጤቶች መረጃ ከመስጠት ባለፈ ወደ ትግበራ ገብተው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከሩ ረገድም አውደ ጥናቱ አስተዋጾው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ተቋሙ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር የማህበረሰብን ህይወት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሻግሩ ሳይንሳዊ፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ ክፍሌ ናቸው።

በዚህም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት መልክ ወደ ተግባር ለውጦ ህዝብን እየጠቀመ እንደሚገኝ ገልጸው

ለአብነት በቡና ልማት አርሶ አደሩ ጋር የደረሱ ስራዎችን አንስተዋል።

አውደ ጥናቱ  ምርምርን ለማህበረሰባዊ ሽግግር ማዋል ላይ ያተኮረ እንደመሆኑ የቀረቡ የጥናት ግኝቶች በተሻለ ውይይት፣ ክርክር መዳበራቸውን ተከትሎ ወደ ትግብራ እንደሚወርዱም ጠቁመዋል።

አውደ ጥናቱ በሁለት ቀናት ቆይታው   ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በውድድር ተሽለው የተገኙ  ጥናታዊ ጹሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ተመራማሪዎች፤ የኢንዲስትሪ ተቋማት ተወካዮች፤ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ኢዜአ ከዲላ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም