ተማሪዎች በሳይንስ እሴቶች ተኮትኩተው እንዲያድጉ ማድረግ ይገባል

396

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) መጋቢት 30/2014 ተማሪዎች በሳይንስ እሴቶች ተኮትኩተው እንዲያድጉ መምህራን እና ወላጆች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን እንዲረጋገጥ በእውቀት የበለጸጉ ዜጎችን ማፍራት እንደሚገባ ተመላክቷል።

"ሳይንስ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊዝክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጥላሁን ተስፋዬ በአውደ ጥናቱ በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርብው ውይይት ተደርጎበታል።

ዶክተር ጥላሁን ሳይንስ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ምክንያታዊና እውነታ ላይ የተመሠረተ ዘርፍ በመሆኑ ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

"ዘላቂ ዕድገት የሚረጋገጠው ሳይንስን በማወቅ ብቻ ሳይሆን በመኖር ነው" ያሉት ዶክተር ጥላሁን፣ ተማሪዎች በሳይንስ እሴቶች ተኮትኩተው እንዲያድጉ መምህራንና ወላጆች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ተማሪዎች በትምህርት የተለማመዱትን በሥራ ላይ ተግባራዊ እንዲያደርጉት የሳይንስ ትምህርቱ ምርምር ተኮር መሆን እንዳለበትም ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ጥላሁን ገለጻ በእውቀት የበለጸገ አዕምሮ በምክንያት የሚያስብ በመሆኑ፣ ዘላቂ ሀገራዊ ልማትን ለማረጋገጥ በአውቀት የጎለበተ አዕምሮ ያላቸው ዜጎች በብዛት መፈጠር ያስፈልጋል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ከዚህ በፊት መንግስት ለትምህርት ተደራሽነት ትኩረት በመስጠቱ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

ይሁንና ይሄ ሀገር አሻጋሪና ምክንያታዊ ትውልድ ከመፍጠር አንጻር የራሱ ክፍተቶች ስላሉበት አሁን ምርምር ላይ ትኩረት መደረጉ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ካሉ ስምንት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱና የመማር ማስተማር ስራውን ምርምር ተኮር ማድረጉንም ዶክተር ዓለማየሁ አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ዋኖ ዋሎሌ እንዳሉት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ለክልሉ ፖሊሲ በግብዓትነት የሚረዱ በርካታ ምርምሮች ጥቅም ላይ ውለዋል።

ለዚህም በጤና፣ በትምህርት፣ በገቢ እና ልማት ላይ አተኩረው የተካሄዱ ጥናታዊ ጽሁፎች ተግባራዊ መሆናቸውን ለአብነት እንስተዋል።

በተፈጥሮ ሳይንስ ቀመር፣ በግብርና እንዲሁም በሕክምናና ጤና ሳይንስ ዘርፎች ላይ ያተኮረውና ነገ በሚጠናቀቀው 158 የጥናትና ምርምር ጽሁፎችም ለውይይት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

በአውደ ጥናት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ  ተመራማሪዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ከስፍራው ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም