ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጀመረው የሬዲዮ ጣቢያ ስርጭት ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻውን እንደሚወጣ አስታወቀ

415

ድሬዳዋ ፤ መጋቢት 30/2014(ኢዜአ) ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ የሬዲዮ ጣቢያ ስርጭት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ በማድረስ ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻውን እንደሚወጣ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከ12  ሚሊዮን ብር በሚበልጥ  ወጪ ያስገነባው የማህበረሰበ አቀፍ ሬዲዮ ጣቢያ ዛሬ የሙከራ ስርጭት ጀምሯል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት  ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን በወቅት እንደተናገሩት፤ ጣቢያው በአራት ቋንቋዎች  ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ መረጃ በማስተላለፍ ሚናውን ይወጣል።

በዚህም እስከ 100 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚሰራጨው ጣቢያ ለሰላም፣ለአንድነት፣ለልማትና ለዕድገት የሚበጁ መልዕክቶች በአፋን ኦሮሞ ፣ በአማርኛ፣ በሶማሊኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንደሚያስተላልፍ አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄዳቸውን ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶች ህብረተሰቡ በአግባቡ ተረድቶ በኑሮውና በአካባቢው ላይ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ ፤ በመጪው ሐምሌ ወር  መግቢያ ወደ መደበኛ ስርጭት የሚገባው የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ ጣቢያው በተለይም ለጋዜጠኝነትና ተግባቦት እንዲሁም የኤሌክትሪክ ምህንድስና ተማሪዎች ቤተ-ሙከራ ያገለግላል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና የተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኢዮብ ነጋ ፤ጣቢያው ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎች ለማፍራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ጣቢያው ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመሆኑ በመረጃ የሚመራ የነቃ ማህበረሰብ በመፍጠር ለሀገርና ለአካባቢ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ  የበኩሉን ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

''ሬዲዮ ጣቢያው በሙያው ብቁና በራስ መተማመን አንግቦ ለመመረቅ ያግዛል'' ያለችው ደግሞ  የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነት የተግባቦት ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሃና ሰይፉ ናት፡፡

ጣቢያው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የሚገጥሟቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተገቢው መንገድ መፍትሄ ያስገኛል ብዬ አምናለሁ ብላለች፡፡

የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሸምሸዲን ደኑር፤ የጣቢያው ሥራ መጀመር ማህበረሰቡንና ዩኒቨርሲቲውን የሚያገናኝና በጋራ ለመስራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ጣቢያው ዘመናዊ የቀረጻ፣ የቀጥታ ስርጭትና የመቆጣጠሪያ ስቱዲዮዎች፣ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ማሰራጫዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም