ሚኒስቴሩ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

107

ደሴ ፤ መጋቢት 30/2014 (ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰበት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ድጋፉን ዛሬ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማት በቴክኖሎጂ ተደራጅተው መልሰው እንዲቋቋሙ ሚኒስቴሩ የበኩሉን ይወጣል።

ለዚህም በአማራና በአፋር ክልሎች በቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጠና መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ ተቋማት እንደጉዳት መጠናቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማጠናከር የሚያስችሉ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ የጽህፈትና የቤተሙከራ ቁሶችን ድጋፍ ሚኒስቴሩ ዛሬ አስረክቧል።

"ድጋፉ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማቀላጠፍ አጋዥ ነው" ያሉት ዶክተር በለጠ፣ ለወልድያ ዩኒቨርሲቲም የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ይዘው መምጣታቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንና ሌሎች  አካባቢ ተፈናቅለው "ድሬ ሩቃ" በተባለ አካባቢ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ፣ የእህልና የአልባሳት ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ ለወሎ እና ለወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች፣ እንዲሁም ለተፈናቃዮች በቁሳቁስ፣ በምግብ እህልና በአልባሳት የሚደረገው ድጋፍ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ነው።

ድጋፉን የተረከቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት ግምቱ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ የዩኒቨርሲቲው ህብት ላይ መዝረፉንና ያልቻለውን ማውደሙን አስታውሰዋል።

ሆኖም ከመንግስት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ድርጅቶች በተደረገ ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው ፈጥኖ በመቋቋም የመማር መስተማር ሥራውን ጀምሯል" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ቀድሞ ወደነበረበት አቅሙ ሙሉ በሙሉ ተመልሶ በተሻለ ደረጃ እንዲሰራ የሚመለከታቸው ሁሉ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ሚንስቴሩ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የተቋሙን የመማር ማስተማር ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያግዝ በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

ሚኒስቴሩ በተጨማሪ በቀጣይ ለአፋር ክልል ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም