በአገራዊ ምክክሩ ሴቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል

90

መጋቢት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በአገራዊ ምክክሩ ሴቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በመሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ለማርገብና ለመፍታት አካታች አገራዊ የሕዝብ ምክክር ማድረግ አስፈልጓል።

ይህንንም ተከትሎ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሰረት፤ አገራዊ ምክክሩን በገለልተኝነት የሚያስተባበርና የሚመራ ተቋም በማስፈለጉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አቋቁሟል።  

ምክር ቤቱ ኮሚሽኑን ለመምራት በሕዝብ ከተጠቆሙ 632 እጩዎች መካከል 42 ግለሰቦች ተለይተው፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የ11 ገለልተኛ እጩዎች ሹመትም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል፤  ኮሚሽኑም በቅርቡ ሥራውን ጀምሯል።  

ይህም አገራዊ ምክክር የታለመለትን ግብ እንዲመታ የሴቶች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው የአዲስ አበባ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ የሚናገሩት።

በመሆኑም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሴቶች የነቃ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የመዲናዋ ሴቶች ይህንን ከግምት በማስገባት ንቁ ተሳታፊ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።

አገራዊ ምክክር መደረጉ የሴቶች ድርሻ የጎላ እንዲሆን ቢሮው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት የተለያዩ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክክሩ ሁሉን አካታችና ፍትሃዊ በማድረግ የተሻለች አገር ለመገንባት ሴቶች ድርሻቸው ከፍተኛ መሆን መገንዘብና ለዚህም መሥራት እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት።

ቢሮውም ሴቶች ንቁ ተሳታፊ ለማድረግ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።  

በተጓዳኝም ምክክሩ ለአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚኖረውን ፋይዳ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የታለመለትን ግብ እንዲመታ ሴቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራውን የጀመረ ሲሆን ከኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል፤ ኅብረተሰቡን በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም