የትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ችግር የመፍታት ጉዳይ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ችግር የመፍታት ጉዳይ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል

መጋቢት 29/2014(ኢዜአ የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ችግር የመፍታት ሥራን የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫው ሊያደርገው እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሔደው ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባው የትምህርት ሚኒስቴርን ያለፉት ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ፤ሚኒስቴሩ ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት ለዜጎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመሰጠት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተጨማሪም በዘርፉ የሚነሱ ተግዳሮቶችን ከመፍታት ባለፈ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ ላይም ጭምር መሥራት እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ውጤት ጋርም ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ቀጣይ ጥያቄ እንዳያስነሱ በጥንቃቄ መሥራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በተቋማቱ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎች ድህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ሥራን ሚኒስቴሩ በትኩረት ሊሄድበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስርም እንዲጠናከር ይበልጥ መሥራትም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባም ዶክተር ነገሪ አሳስበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በበኩላቸው እንደ አገር ችግር የሚስተዋልበትን የትምህርት ጥራት ችግር ለማሻሻል መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዚህም ማኅብረሰቡ፣ ወላጆች፣ የምክር ቤት አባላትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ድጋፉቸውን ማድረግ እንዳለባቸውም በመጠቆም።
የፈተናን ስርቆት ለማስቀረት በታብሌት እንዲሰጥ ለማድረግ አንድ ሚሊየን ታብሌት ለመግዛት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በየትምህርት ቤቱ ፈተና ከመስጠት ይልቅ ሁሉንም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲፈተኑ ለማድረግ አንደ አንድ አማራጭ መታሰቡን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከከፍተኛ ትምህርት ከማጠናቀቁ በፊት የመውጫ ፈተና COC ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ትውልድን በጥራት ከማፍራት አንጻር ያለውን የጥራት መጓደል ለማሻሻል በፍኖተ ካርታ ጥናት የሥርዓት ትምህርት ለውጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከ1ኛ እስከ 12ኛ ተከልሶ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርትን በ2014 ዓ.ም ሙከራ ለማካሄድ ታቅዶ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል በ589 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሙከራ ትግበራ እየተካሄደ ሲሆን በ2015 ዓ.ም ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል ብለዋል።
በ89 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙከራ በ2015 እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቶች የሚታየውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ውስንነት ለመፍታት የሚያስችል ስልቶች በቀጣይ እንደሚተገበርም ጠቁመዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወቅቱ በሚጠይቀውና ተልዕኮውን በሚመጥን መልኩ በየደረጃው ያለው አመራር በአቅምና በአመለካከት ሙሉ ቁመና እንዲኖራቸው ሥልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ስርቆት በተደጋጋሚ እየተከሰተ መምጣቱን ለምክር ቤቱ ገልጸው ችግሩን ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አንዳንድ አካላት ፈተናውን በማህበራዊ ሚዲያ በመልቀቅ ሁሉም ተፈታኝ እንዲያገኝው በማድረግ የትምህርቱን ስርዓቱን በማናጋት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉም ነው ያመለከቱት።
ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የትምህርት ዘርፉንና ፖለቲካውን ለያይቶ ያለማየት ችግሮች የሚያመጡት በመሆኑ በቀጣይ እርምት ሊወሰድበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።
ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቶች የመሰረተ ልማት ፍላጎትን ለሟሟላት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ተማሪዎች በብቃታቸው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በራሳቸው እውቀት አጥንተው ፈተናን እንዲያልፉ የማድረግ ሥራ ላይ ብዙ ርቀት መሔድ እንደሚያስፈልግም ነው ዶክተር ብርሃኑ የጠቆሙት።