ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን - የሃይማኖት አባቶች

114

ሶዶ፤ መጋቢት 29፣ 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲሳካ የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የወላይታ ዞን የሃይማኖት አባቶች አስታወቁ። 

የኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሀይማኖት አባቶች ሀገራዊ ምክክር የመንግስት ወይም የፓርቲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ በመሆኑ በመረዳት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዞኑ የእስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሐጂ ናስር የሱፍ የሃይማኖት ተልዕኮ በዋናነት ሰላም ማስፈን በመሆኑ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

"የምክክር መድረኩን ፖለቲካዊ ይዘት ማላበስ ተገቢ አይደለም" ያሉት ሐጂ ናስር "በሃይማኖታዊ አስተምህሮ በኩል ለምክክሩ ውጤታማነት  ድርሻዬን እወጣለሁ" ብለዋል።

ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ዜጎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

መንግስት ዘላቂ ሰላም ለመገንባትና ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉም ሐጂ ናስር አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የወላይታ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከሰላም ቀሲስ ቦክቻ ኤንጋ በበኩላቸው''ሰላም የሚመጣው በመመኘት ብቻ ሳይሆን፣ ለሰላም መስፈን በመትጋት ነው" ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ቁርሾዎችን በማስወገድ ለቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊ ሀገር ለማስረከብ አስተዋጾው የላቀ በመሆኑ ስኬታማ እንዲሆን ሚናቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

''ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ አይደለም'' ያሉት መላከሰላም ቀሲስ፣ "ስለምክክሩ የማይመለከተው ዜጋ እንደሌለ ታውቆ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የምዕመናን አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላም እንዲቆሙ  በሃይማኖቱ አስተምህሮ በመገንባት ለምክክሩ ስኬታማነት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

የወላይታ ዞን ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሰብሳቢ መጋቢ ጊዮርጊስ ጎአ በበኩላቸው ህዝቡ የሀገራዊ ምክክሩን ዓላማ በመረዳት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

"ምክክሩን እንደ እድል በመጠቀም የሰላምና አብሮ የመኖር እሴቶችን ለማጠናከር ኃላፊነቴን እወጣለሁ" ብለዋል።

"የሀይማኖቱ አስተምህሮ በሚፈቅደው መሰረት በማህበረሰቡ መካከል የቆዩ የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶች እንዲጎለብቱ በማስተማር ለምክክሩ ስኬታማነት ድርሻዬን እወጣለሁ" ሲሉ አክለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት በየአስተምህሮታቸው ስለ ሰላምና አብሮነት በማስተማር በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያቋቋመችው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራውን ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ይፋ መደረጉ ይታወቃል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም