በክልሉ ከ45 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የተፋሰስና የእርሻ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል--ቢሮው

78

ጋምቤላ መጋቢት 29/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ45 ሺህ ሄክታር ተፋሰሶችና በተራቆቱ የእርሻ መሬቶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

በሌላ በኩል በክልሉ ዘንድሮ ለተከላ በመዘጋጀት ላይ ካሉት ችግኞች መካከል 75 ከመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ቡሮው ለኢዜአ አስታውቋል።

በጋምቤላ ክልል በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ45 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ  ስራዎች መከናወኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኮዌት ሉል አስታውቀዋል።

በክልሉ ካለፈው ጥር 2014 ዓም አጋማሽ ጀምሮ ለሁለት ወራት የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች መከናወኑን  ለኢዜአ ገልጸዋል ።

የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራው በ21 ሺህ 801 ሄክትር በሚሸፍኑ 153 ተፋሶችና በ23 ሺህ 449 ሄክታር በጎርፍ የአፈር መሸርሸር ባጋጠመው የእርሻ መሬት ላይ መከናወኑን  ምክትል ሃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ እንደተሳተፈ ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል ።

በበጋ ወራት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስተራዎችን በአረንጓዴ ተክሎች ለማላበስ የችግኝ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በመጪው ክርምት ለሚካሄደውን 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጨምሮ በ68 ጣቢዎች ከ9 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ የችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ ነው" ብለዋል።

በመዘጋጀት ላይ ካሉት ችግኞች መካከል 75 ከመቶ የሚሆኑት የማንጎ፣ የአቡካዶ፣ የዘይቱናና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ምክትል ኃላፊው እንዳሉት በአረንጓዴ ልማት ስራ የሚለሙ ተፋሰሶች ላይ ችግኝ  ከመትከል ጀምሮ ጸድቆ የሚፈለገውን ጠቀሜታ እንዲያስገኝ  የክትትልና የእንክብካቤ ስራ ከህብረተሰቡ ይጠበቃል።

በቀጣይ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እያጋጠመ ያለው የችግኝ መድረቅ እንዳይከሰትና የመጽደቅ መጠንን ለማሳደግ  የእንክብካቤ ስራ ከባለድርሻ  አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም