ገበያውን ለማረጋጋት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የቅንጦት እቃዎችን መቀነስና በመሰረታዊ ፍጆታዎች ትኩረት ማድረግ አለበት

አዲስ አበባ መጋቢት 29/ 2014 (ኢዜአ) መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ለቅንጦት እቃዎች የሚወጣውን ወጪ በመቀነስ በመሰረታዊ ምርቶች ላይ ፈሰስ ማድረግና ድጎማውን ማስፋት እንደሚገባ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ የባለፉት ወራት የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ያሳያል።

ይህ የዋጋ ግሽበት በተለይም በምግብ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ነው መረጃው ያመላከተው።   

ይህንንም ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሙያዎቹ እንደገለጹት፤ መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ የአጭርና የረጅም ጊዜ እርምጃዎች መውሰድ ይገባዋል ብለዋል።    

በተለይም ከውጭ የሚገቡትን የቅንጦት እቃዎች በመቀነስ ለእነዚህ እቃዎች የሚወጣውን የውጪ ምንዛሬ በመሰረታዊ እቃዎች ላይ መዋል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የፍጆታ እቃዎችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት መንግሥት የሚያደርጋቸው ጥረቶች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ምከረ ሃሳባቸውን የሰጡት።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማኅበር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ስሜነህ ቢሴ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት የዋጋ ንረቱን ለማቃለል ከውጭ በሚገቡ የቅንጦት እቃዎች ላይ ተጨማሪ ታክስ መጣል ያስፈልጋል።

በአንጻሩ በመሰረታዊ በሆኑ የፍጆታ ምርቶችን ላይ የተጣለውን ታክስ ደግሞ ዝቅ በማድረግ የሸቀጥ ዋጋን ማረጋጋት እንደሚቻልም ምክረ-ሐሳባቸውን ለግሰዋል።

ይህ መፍትሔ ደግሞ በመንግሥት ሊወሰድ የሚችል የፊስካል ፖሊሲ እርምጃ መሆኑንም በመጠቆም።

በአገሪቱ ሰላምን ማረጋገጥና ምርትን በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የሚወሰድበትን መንገድ ማጠናከርም ሌላው መፍትሔ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አምራች የሆነው ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችንና የሥራ እድሎችን ማመቻቸት ላይም ማተኮር ችግሩን ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንግሥት ተቋማት ወጪያቸውን እንዲቀንሱ ማድረግ፣ የአነስተኛ ጥቃቅን አምራቾችን ማጠናከርና የመግስትና የግል ሴክተሩን ግንኙነት ማጎልበትም እንዲሁ መፍትሔ መሆኑን አንስተዋል።

ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በአይነትና በጥራት ማሳደግ፣ በዘርፉ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ገቢራዊ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያና አማካሪው አቶ ደረጀ ደጀኔ ፤በበኩላቸው የቅንጦት ምርቶችን በስፋት ከውጪ ማስገባት ለመሰረታዊ ፍጆታዎች መናር ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለቅንጦት ምርቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በመቀነስና በቀጥታ ለፍጆታ ምርቶች ግዥ እንዲውል በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአገር ውስጥ የፍጆታ ምርትን ማሳደግን ጨምሮ ከውጭም በስፋት እንዲገቡ በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በአገር ውስጥ ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

አምራቹ ባለው ውስን ቦታዎች ላይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ እርምጃዎችም መወሰድ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ለኅብረተሰቡ መድረሳቸውን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ማሳሰቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም