በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር የምክክር መድረክ ይካሄዳል

132

መጋቢት 28/2014/ኢዜአ/ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር የምክክር መድረክ እንደሚካሔድ አስታወቀ።

የምክክር መድረኩ ፓርቲው በቅርቡ ከመጋቢት 2 ቀን እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓም ባካሔደው ጉባኤ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫን አስመልክቶም ነው ከወጣቶቹ ጋር ምክክር የሚያካሒደው ተብሏል።

መድረኩ በልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ፓርቲው ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በመላው አገሪቱ የሚካሄደውን ምክክር ለሚመሩና ለሚያስተባብሩ ወጣቶች ገለፃ አድርጓል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊና ምክትል ፕሬዚደንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ፤ በመላ አገሪቱ እስከ ወረዳ ባሉ ከተሞች የወጣቶች መድረክ ይካሄዳል ብሏል።

ለምክክሩ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ከተሞች ተመርጠው መድረኩን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጿል።

በቀጣዩ ቅዳሜ የሚካሔደው ይኸው የመጀመሪያው ዙር መድረክም በተመረጡ 18 የአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች ላይም እንደሚሆን አብራርቷል።

የንቅናቄ መድረኩ እስኪጠናቀቀም ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉም ነው የጠቆመው።

ፓርቲው በጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች በሚመለከት ከወጣቱ ጋር ተግባቦት መፍጠር ዋነኛ ዓላማና የመድረኩ አጀንዳ መሆኑንም አመላክቷል።

በውይይቱ ከወጣቱ የሚነሱ ገንቢ ሃሳቦች ለፓርቲው ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ግብዓት እንዲሰጥ ለማስቻል እንደሚረዳም ነው የተገለፀው።

የብልጽግና ፓርቲ የፓለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ፤ ኢህአዴግ ለህዝብ ጥያቄ አፋጣጫ ምላሽ ባለመስጠቱ ውድቀቱን እንዳፋጠነው አስታውሰዋል።

አሁን ያለው መሪ ድርጅትም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ህዝብን የሚያማርሩ ብልሹ አሰራሮችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ምላሽ ለመስጠት የገባውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም አካላት የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የወጣቶች የንቅናቄ መድረክ የሚመሩ አካላት በበኩላቸው ቀጣይ በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር የሚደረገው መድረክ የሚነሱ ጥያቄዎች የተሻለ አረዳድ በመያዝ ወደ ልማትና መልካም አስተዳደር ስራ ለመግባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

መድረኩም የወጣቱን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሳደግ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረትን ለመደገፍ እንደሚረዳም ነው የተመለከተው።

በመድረኩም የወጣቱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን በሚመለከት ሐሳቦች ተነስተው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ይጠበቃል ተብሏል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም