መታወቂያን ጨምሮ ሌሎች የሀሰተኛ ማስረጃዎች እየተበራከተ መምጣት ለአገልግሎት አሰጣጡ ፈተና ሆኗል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28/2014 /ኢዜአ/   የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ሀሰተኛ መታወቂያ፣ የጋብቻ ምስክር ወረቀትና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣት ለአገልግሎት አሰጣጡ ፈተና እንደሆነበት ገለጸ ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴና የአገልግሎት አሰጣጥ ጎብኝተዋል።

አገልግሎቱ ከተቋቋመበት 1938 ዓ.ም ጀምሮ የተለያየ ስያሜ እየተሰጠው እዚህ ቢደርስም እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ የማስተናገድ አቅሙ በቀን ከ30 ሰው እንደማይበልጥ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ለረዥም ዓመታት መልካም ስም የሌለው አገልግሎት መስጫ ተቋም ተምሳሌት ሆኖ የዘለቀውን ስሙን በማደስ በ15 ቅርንጫፎቹ  በ50 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች በቀን እስከ 6 ሺህ ባለጉዳዮችን ማስተናገድ መጀመሩም ተነስቷል።

አገልግሎቱ በሁሉም ቅርንጫፎች ወጥ የሆነ ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ አድርጓል ነው  የተባለው።

በመሆኑም 75 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎቶች በ'ኦን  ላይን' እየተሰጡ መሆኑም ተገልጿል።

አገልግሎት ፈልገው በተቋሙ የነበሩ ባለ ጉዳዮችም ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ መሆኑን መስክረዋል።

ተገልጋዮች አስፈላጊ መረጃዎችን አሟልተው ከቀረቡ አገልግሎቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ማግኘት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

የአገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ እንዳሉት፤ በዚህም አገልግሎቱ ከሚያስፈልገው 1ሺህ 400 የሰው ሃይል ባለሙያ አሁን ያለው 8 መቶ ወይም 58 በመቶ ብቻ መሆኑን ነው።

ተቋሙ በሚችለው አቅም አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ከሚያዚያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሰራተኛ ቅጥር፣ ዝውውርና የደረጃ እድገት እንዳይፈጽም ተከልክሏል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ለተቋሙ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ከደመወዝና ከህንፃ ኪራይ የሚተርፈው በጀት ከ15 በመቶ አይበልጥም።

በወረቀት የተሰሩ መረጃዎችን ወደ ዲጂታል የመረጃ ቋት ለማስገባት የሚያስፈልግ መሳሪያ ወይም ስካነር እጦት ሳቢያ ስራውን በአግባቡ መስራት አልተቻለም ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ፤ ተቋሙ በርካታ ባለጉዳዮችን የሚያስተናግድ በመሆኑ በቂ የሰው ሃይል ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል ችግሩን እንዲፈታ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጥሩ የሚሰራን ተቋም መንግስት ማበረታታት ስላለበት ያለውን የፋይናንስ ውስንነት ለማስተካከል የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ብለዋል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃ እየተባባሰ በመምጣቱ በስራቸው ላይ ጫና መፍጠሩን አክለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 231 ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎችን መያዛቸውን ገልጸው፤ 152ቱ ሀሰተኛ መታወቂያ 26 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ያላገባ ማስረጃ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወንጀሉ አድማሱን እያሰፋ ሀሰተኛ የቦታ ካርታ ሁሉ እየተዘጋጀ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ክልሎችም ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ በክፍያ ስርዓት ላይ ያለው የሰዎች መጉላላት መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ገልጸው፤ የሀሰተኛ ሰነድ ማስረጃዎችን ለመከላከል ከክልሎች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም