ጊዜውን የዋጀ የሁሉንም ተሳትፎ የሚሻ ሃገራዊ ጉዳይ - ኢዜአ አማርኛ
ጊዜውን የዋጀ የሁሉንም ተሳትፎ የሚሻ ሃገራዊ ጉዳይ
ጥቂት ሳምንታት በፊት ቁጥር 1265/2014 የሚል ስያሜ የተሰጠው አዋጅ [1]ኢትዮጵያ የተሸከመቻቸውን አገራዊ ችግሮች በምክክር ለመፍታት ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና የተራራቁ ሃሳቦች አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ንግግሮች እንዲቀራረቡ ለማስቻል ለተቋቋመው ኮሚሽን የተሰጠው ህጋዊ እውቅና ሲሆን ኮሚሽኑ ከምስረታው በፊትም ሆነ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
አስተያየቶቹ ገንቢ የመሆናቸውን ያክል በተለያየ አረዳድ የያዘውን ዓላማ ያላገናዘበና ብዙም አስተማሪነት የሌላቸው የተሰሳቱ ቅድመ ትንበያዎችም የመታይባቸው ናቸው። ለዚህ ደግሞ አሁንም የኮሚሽኑን ሃላፊዎችን ጨምሮ የህግና የፖለቲካ ምሁራንን ተደጋጋሚ ግልጽና በተጨባጭ ማሳያዎች የታገዙ ማብራሪያዎች የሚፈልጉ ጥያቄዎች በብዛትና በአይነት መሰንዘራቸው ከሂደቱና ከኮሚሽኑ አዲስነት አኳያ የሚጠበቅም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ኮሚሽኑ በተመሰረተ ሰሞን የኮሚሽኑ አባላት ለህዝብ ይፋ መደረጋቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ኮሚሽኑን የተመለከቱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፋ ያሉ ማብራሪያ ሲሰጡ ሃገረመንግስታት ሲገነቡ ሁሉንም አይነት አማራጮች፣ ድርድርም ሆነ ሃይል ጥቅም ላይ መዋላቸውን ታሪክን አጣቅሰው በማንሳት ይሄ ኮሚሽን እንዲቋቋም ያስፈለገው ኢትዮጵያን ለማጽናት ነው ማለታቸው ይታወሳል።
አገራዊ ውይይቶች የአንዲት ሃገር ህልውና በአንድ ወይም በሌላ መንገድ አደጋ ላይ ሲወድቅ አሊያም ዜጎችና ይመለከተናል የሚሉ አካላት የሃገሪቱ ቀጣይነትና የዜጎች የወደፊት ኑሮ ሲያሳስባቸው የሆነ አይነት የመውጫ ብልሃት ለመሻት የአኗኗር ዘይቤያቸውን፣ የፖለቲካና ኤኮኖሚ አወቃቀራቸውን ያሉበትን ክፍለአለም ታሳቢ ያደረገ አካታች የንግግር የውይይት ወይም የድርድር መንገዶች ስለመፈለጋቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
እነዚህ ሰላማዊ የግጭት መፍቻ (ሊከሰት የሚችልን የግጭት ስጋት ማስወገጃ)መንገዶች በመሆናቸው አገራዊ ውይይቶችንም ሆነ ምክክሮችን ገደብ ሳያስቀምጡ አካታች አሳታፊና ቀናነትን በተላበሰ መንገድ ማድረግ የሚቻል ከሆነ በርካታ ትሩፋቶች እንደሚኖሩት የሚናገሩት የዘርፉ ምሁራን ሰላማዊ ንግግር በባህሪው ራስን በሌሎች አካላት ቦታ በማስቀመጥ “በተከፈተ ልብ ሌሎች ምን ይላሉ?” የሚለውን በቀላሉ ለመገንዘብ እንደሚያስችል ይናገራሉ።
የሰላማዊ ውይይት ባህል መዳበር ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ ከህዝቡ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተቀራረበ የዲሞክራሲ ባህል ለመገንባት ግዴታውን እየተወጣ በመብቱ የማይደራደር ትውልድ ለመፍጠር አይነተኛ ድርሻ እንዳለው የሚያተቱት እነዚህ የግጭት አፈታት ምሁራን ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሃገራቸውን አጽንተው ያቆዩባቸው የግጭት አፈታትና ሰላም የማስፈን ስርአቶች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ የሚታሰበው እንደሚመጣ እምነታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የፖለቲካና የህገመንግስት ምሁራን ሃገራዊ ውይይቶችና ምክክሮች በሁሉም የሃገሪቱ አከባቢዎች ሁሉንም ዜጎች የሚመለከትና ያለምንም አድልዎ የሚያሳትፍ የሃሳብ ልዩነትን የሚያከብር ነው ቢባልም ከእያንዳንዱ ሰፈርና መንደር ይልቅ ግልጽና ሚዛናዊ በሆነ የስብሰባ አመራር ስነስርአት የሃገር ህልውናና ቀጠይነት ላይ ትኩረት በመስጠት ዋና ዋና ሃገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀትና በስፋት ለማየትና ሃሳብ ለማዋጣት እንደሚግዝ ያብራራሉ።
“አንድ ሚሊዮን ሀሳቦች ቢኖሩ አንድ ሚሊዮኑን ጠረጴዛ ላይ ለማምጣት እንኳን በተሰጠን ሦስት ዓመት ጊዜ ቀርቶ በ30 ዓመትም ላንጨርሰው እንችላለን” ያሉት የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ [2]“አገራችን ለሁላችንም እኩል እንድትሆንና ወደፊት በሚገባ በአስተማማኝ ሁኔታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሻገርና እንድትቀጥል ከተፈለገ ሁሉም ተባባሪ ሊሆን ይገባል” በማለት አጽንኦት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም ሲባል የተመሰረተው አገራዊ የምክክር መድረኩ ቀደምሲል የነበሩና አሁንም ፈተና ሆነው የተገኙ የአገራችንን ችግሮችን ተነጋግሮ ከመፍታት አካያ የሚኖረው ሚና ጉልህ ስለመሆኑ ከወዲሁ እየተነገረለት ሲሆን ማንኛውም ችግር የተፈጠረው ሰዎች በሃሳብ ባለመግባባታቸው በመሆኑ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ችግራቸው እንዲወገድ በቅድሚያ መነጋገር እንዳለባቸው የሚያመለክቱ አስተያየቶችም እየተሰጡ ነው።
በዋናነትም ፖለቲካና አስተዳደሩን የተመለከቱና በዘመናዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥረዋል የተባሉ ችግሮች መነሻቸው “ሃሳብ አለን አሊያም ዘመናዊ ትምህርት ቀስመናል” ያሉ ሰዎች የፈጠሯቸው አሊያም ያባባሷቸው እንደሆኑ የሚገለጽ ሲሆን “ችግሩን ማወቅ የመፍትሄው ግማሽ ነው” እንደሚባለው ሃሳብ አለን የሚሉቱ እንዲናገሩ ብቻም ሳይሆን እንዲመካከሩ የተጀመረው ጥረት ለሃገር ህልውና ሲባል መደረጉ የግድ ነው።
ሁሉንም ዜጋ ያሳተፋል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምክክር መድረኩ ከጾታ ከኑሮ ዘይቤ፣ ከትምህርት ደረጃ ከሃብት መጠን፣ ከሃይማኖትና እምነት፣ ከቋንቋና ከመሳሰሉት የልዩነት ግንቦች ወጥቶ አካታች ሊሆን ይገባል የሚሉ አሰታየቶች ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ከመሰንዘራቸው ጎን ለጎን ሃገራዊ ምክክሩ “ራሱን የፖለቲካ ምሁርና ልሂቅ አድርጎ በሚያቀርበው ብልጣብልጥ እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ይገረግ” በማለት ሃሳብ የሚሰነዝሩም አልታጡም።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባሏ አምባሳደር አይሮሪት መሓመድ [3](ዶክተር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ “አገርን ያሻግራል የሚል ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ ሴቶች በምክትል ኮሚሽነርነትና በአባልነትም ተካተዋል። ይህም ሴቶች በወሳኝ ኃላፊነቶች ላይ ቢመደቡ ውጤታማ መሆን ይችላሉ የሚል ዕምነት መጣሉን ያሳያል”ሲሉ ገልጸው ሴቶች የሕብረተሰቡ ግማሽ አካል በመሆናቸው[4] ኢትዮጵያን በተመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ የማይሳተፉ ከሆነ እንደ አገር የሚታሰበው ልማትና ዴሞክራሲም ሊመጣ እንደማይችል አስረድተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚልኳቸው ተወካዮች፣በህብረተሰቡ ዘንድ ቅቡልነት ያላቸው ግለሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ታዋቂ ምሑራን፣ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ለሚያውቁት እና ለሚያውቃቸው ኅብረተሰብ ሰላም አንድነትና ብሩህ ተስፋ ሲባል የምክክሩ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ የሚጠይቁ ያሉትን ያህል የተጠቀሱት ሰዎች አስማሚ ተክለስብእና የላቸውም አሊያም በሆነ ምክንያት “እምነት የማይጣልባቸው በመሆኑ ሊወክሉን አይችሉም” የሚሉ ድምጾች ሊሰሙ እንደሚችሉም እሙን ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩትና የሰላምና ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ሰሞኑን በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሰላምና ጸጥታ ተመራማሪው ዶክተር ሰሚር የሱፍ እንደተናገሩት “የአገራዊ ምክክር መድረኮች በተለያዩ አገሮች ተካሂደዋል፤ ውጤት እንዲያገኙ ያደረጋቸው አገራዊ ምክክሩን የሚያካሂደው አካል ቅቡልነት ነው” ብለዋል።[5]አገራዊ ምክክር አድርገው ያልተሳኩላቸው አገሮች ብሔራዊ ምክክሩን የሚያስኬደው አካል ከኅብረተሰቡና ከምሁራን ቅቡልነት በማጣቱ እንደሆነም አስረድተዋል።
በዚህ ሂደት እንሳተፋለን የሚሉ አካላትም ኢትዮጵያም የተሳካላቸውን እና የከሸፈባቸውን ሃገራት አገራዊ የምክክር ተሞክሮዎች በስፋትና በጥልቀት በማጥናት [6]ከራሷ አውድና ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስማማት እንደሚኖርባት ያሰመሩበት ተመራማሪው ሂደቱ ተስፋና ስጋት የተቀላቀለበት በመሆኑ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ሃገራዊ አጀንዳ ስኬት ላይ እንዲያደርስ ካስፈለገ መንግሥትና ይመለከተናል የሚሉ አካላት ኮሚሽኑ በሚገባው ልክ ድጋፍ እንዲያገኝ አበርክቷቸው ላቅ ያለ መሆኑን አስታውሰዋል።
የሃገሪቱን ዋናዋና ችግሮ ነቅሶ በማወጣት የመፍትሄ አማራጮች እንዲፈለጉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሎ የሶስት አመታት ቆይታ እንዲኖረው የተቋቋማው ይሄ ኮሚሽን ዋነኛ ተግባሩ የምክክር መድረኮችን ማመቻቸትና ሰላማዊ ምክክርን ለምልአተ ህዝቡ ማለማመድ ከዚያም የዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን በመገንዘብ እና ጎጂ ከሆኑ ፍረጃዎችና አፍራሽ አስተያየቶች በመቆጠብ [7]ይመለከተኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድጋፍና ትብብር በማድረግ ለስኬቱ መረባረብ ይኖርበታል።
የሚዘጋጀው አገራዊ የምክክር መድረክ ለታይታና ለይስሙላ የሚከናወን ሳይሆን የሃገሪቱን ችግሮች ካለችበት ውስጣዊና ውጫዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ እንደዜጋ የጋራ ሃገራችንን ከተጋረጠባት አስፈሪ ሁኔታ ለማውጣትና ትክክለኛና ሰላማዊ ጎዳና ላይ ለማራመድ ድርሻችንን የምናበረክትበት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በሃላፊነትና በያገባኛል መንፈስ ሊሳተፍና ታሪካዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
[1] https://www.bbc.com/amharic/news-59822579
[2] https://www.press.et/?p=67319
[3] https://www.press.et/?p=68161
[4] https://africanarguments.org/2022/03/ethiopias-national-dialogue-commission-where-are-the-women/
[5] https://press.et/herald/?p=51783
[6] https://www.ethiopia-insight.com/2022/03/12/ethiopias-stillborn-national-dialogue/
[7] https://addisstandard.com/news-national-dialogue-commission-failed-before-formation-balderas-party/