ሁላችንም ለሰላም መረጋገጥ ልንተጋ ይገባል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ

85

ጎንደር (ኢዜአ) መጋቢት 25/2014 --ሰላም የሁሉም መሰረትና ዋጋውም የማይተመን በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም መረጋገጥ ልንተጋ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስገነዘቡ፡፡

የጎንደርና አካባቢው ህዝቦችን የአብሮነት የጋራ እሴቶች የሚያጠናክር የሰላም እና የልማት ህዝባዊ የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የተለያዩ አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።  

የውይይቱ ዋና ዓላማ በጎንደር ቀጠና ሁሉንም የሰላም አማራጮች አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል ህዝባዊ መነሳሳት ለመፍጠር መሆኑን ዶክተር ይልቃል ገልጸዋል።

"ሰላም የሁሉም መሰረትና ዋጋውም የማይተመን በመሆኑ ለሰላም መረጋገጥ ሁላችንም ከልብ  በመነሳት ልንተጋ ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

በተለይ የክልሉን ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ለማጠናከር ሰላም ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለተግባራዊነቱ ሁሉንም ጊዜ ተጠቅሞ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው፣ "ህዝቡ ለህልውና ዘመቻው ያሳየውን ያልተቋረጠ ተሳትፎ በሰላምና ልማት ግንባታ ሊደግመው ይገባል" ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከአመራሮች በተጨማሪ ከጎንደር ከተማ፣ ከሰሜን፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም