ህዝብን ያማረሩ አመራሮችን በመለየት መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

69
ደብረ ብርሃን ነሃሴ 30/2010 የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠር  ህዝቡን ያማረሩ አመራሮችን በመለየት መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ በሰሜን ሸዋ  አጎለላና ጠራ ወረዳ እና ደብረብርሃን ከተማ  ነዋሪዎች ጠየቁ። ለውጡንና ልማቱን ለማስቀጠል የተቋቋመው ጊዜያዊ  የህዝብ አስተባባሪ ኮሚቴ ነዋሪዎችንና   አመራሩን አወያይቷል፡፡ በውይይቱ ወቅት የከተማው ነዋሪ የመቶ አለቃ ከፈለኝ ወልደጻዲቅ እንዳሉት የተጀመረዉን ለውጥ ለማስቀጠል ጉድለት በሚታይባቸው አመራሮች እርምጃ በመውሰድ ሊያስተካክል ይገባል፡፡ አሁን ያሉ የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የወጣቱ የሥራ እድል ፈጠራ ችግር፣ በቀበሌ የሚስተዋለው  ደካማና ቅንነት የጎደለው የአገልግሎት አሰጣጥ በፍጥነት መታረም እንዳለበት አመልክተዋል። በዞኑ የአመራር ሹመትና አወቃቀርም በዝምድና እንጂ  ብቃትና እውቀትን ያገናዘበ ባለመሆኑ  መንግስት አመራሩ ፈትሾ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ  አቶ ሰጠው  ደምሴ በበኩላቸው ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም  የወከላቸውን ህዝብ እየበደሉ ለግል ጥቅማቸው የሚሯሯጡ አመራሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠር  ህዝቡን ያማረሩ አመራሮችን በመለየት መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል። ጊዜያዊ የህዝብ አስተባባሪ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ አማረ አሰፋ መንግስታና ህዝቡን አቀራረበው  በማወያየት ችግሮችን ለመፍታት ኮሚቴው መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡ ወጣቱንም በመምከር የመልካም አስተዳደር በደሎችንና የልማት ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ለህዝቡ ተጠቃሚነት እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ በአጎለላና ጠራ ወረዳ ጫጫ ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከተሳተፉት መካከል   ወጣት አዲሱ ሃይለስላሴ  እንዳለው በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ የህዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ አመራሮች ሊመደቡ ይገባል፡፡ ባለፉት ዓመታት ለወጣቶችና ለሴቶች በቂ የስራ እድል እየተፈጠረ ያለመሆኑን እና በመንግስት መስሪያ  ቤቶች ፈጣን አገለግሎት ነዋሪዎች እያገኙ ባለመሆናቸው የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ሲፈጠሩ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ባለፉት ጊዜያት የብጥብጥ ችግሮች መፈጠራቸውን ጠቁሞ፤"አሁን ከችግሩ በመመለስ እንደገና የለውጥ ሂደት በመሆኑ ይህን ተቀብሎ የሚያስቀጥል አመራር ያስፈልጋል "ብሏል። አቶ ደምረው ከበደ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው በሃገሪቱ አሁን የመጣው ለውጥ እንደሚደግፉ  ጠቁመው፤ እስከ ቀበሌ ያለው አመራር ተፈትሾ ከለውጡ ጋር የሚጓዝ ብቁ መሪ መኖር እንዳለበት ጠቁመዋል። በደብረ ብርሃን መድረክ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ  ለውጡን የማይደግፉና የአሰራርም ሆነ የአመለካከት ጉድለት የሚታይባቸዉን አመራሮችም በመለያት እርምጃ እንደሚወስዱ አረጋግጠዋል፡፡ " የሚነሱ የመልካም አስተዳር፤የልማት ጥራትና ሌሎች ጉድለቶችንም በአጭር፤በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ዕቅድ ከህብረተሰቡ ጋር ለመፍታት እንሰራለን "ብለዋል፡፡ የተጀመረው ለውጥ በጥቅመኞች እንዳይደናቀፍ ለህዝቡ፣ወጣቱና የኃይማኖት አባቶች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥም መዕልክታቸውን  አስተላልፈዋል፡፡ በጫጫ ከተማ ውይይት ላይ የተገኙት የዞኑ ምክትል አስተዳደሪ አቶ ብርሃኑ ታየ እንዳሉት በህዝብ የተነሳውን ቅሬታ ለመፍታት ከለውጡ ባለቤት ህዝቡ ጋር  በትኩረት ይሰራል፡፡ በቀጣይ ከቀበሌ አስከ ወረዳ ባለው ደረጃ ህዝቡን በማሳተፍ ለውጡን ሊያፋጥኑ የሚችሉ መሪዎችን እንደሚመደብም  አረጋግጠዋል፡፡ በደብረ ብርሃንና ጫጫ ከተሞች በተካሄደው ህዝባዊ ውይይትም ከሁለት ሺህ በላይ ህዝብ ተሳትፏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም