ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

140

አዲስ አበባ፣  መጋቢት 24/ 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የኮንፈረንስ (MICE) ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ለማስቻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአገሪቱ ትላልቅ መስህብ ባላቸው አካባቢዎች የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎችን በማጠናከር ምቹ የቱሪስት መናሃሪያ የማድረግ ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ሃብት ያላት በመሆኑ እነዚህን ሃብቶች የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ከተቻለ በቀዳሚዎቹ የቱሪዝም መዳረሻ አገራት ተርታ መሰለፍ ትችላለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የኮንፈረንስ (MICE) ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን የማስቻል ተግባራትም በመከናወን ላይ መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አገራዊ፣ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖራት እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ኩነት መዳረሻ እንድትሆን ለማስቻል ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

አፍሪካዊያንም ሆኑ ሌሎች የዓለም አገራት የተለያዩ ሁነቶች፣ ኤግዚቢሽኖችና ስብሰባዎችን በኢትዮጵያ ማዘጋጀት እንዲችሉ ጉዳዩን ሊያሳልጥ የሚችል ቢሮ ተቋቁሞ ወደ ስራ ለመግባት ጥረት እየተደረገ እንዳለ ጠቁመዋል። 

በአሁኑ ወቅት ቱሪዝሙን ዲጂታል በሆነ መንገድ የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በተለያዩ አገራት የሚኖሩ አምባሳደሮች የኢትዮጵያን ቱሪዝም እንዲያስተዋውቁ ስልጠናዎች እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የቱሪዝም ዘርፉን ለማጠናከር እንዲያስችል የፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ገልጸዋል።

የቱሪዝም ኢንቨስትመንት መገለጫዎችን በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች የማድረስ እና የማስተዋወቅ ስራ እየተተገበረ እንደሆነም አስረድተዋል።

የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ተቀርጾ ያለቀ ሲሆን ይህም የኢንቨስትመንት ስራው ከዚህ ቀደም ለመንግስት እና ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለውጭ ባለሃብቶች የነበረውን አሰራር በመቀየር የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሃብቶች እኩልና ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ እንዲሳተፉ እድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን ለማጠናከር የቱሪዝም መዳረሻ ልማት እቅዶች ተይዘው እየተሰሩ እንዳሉም ጠቁመዋል።

በመላ አገሪቱ በተለይ በዋና ዋና የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል የመስህብ አቅም ባላቸው ቦታዎች ላይ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎችን በማከናወን የቱሪስት መናሃሪያ እንዲሆኑ ለማስቻል ታስቦ እየተሰራባቸው ያሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመሰረተ ልማት ማሟላት፣ በአካባቢው ላይ ለቱሪስቶች የሆቴል እና ሎጅ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማጠናከር፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጥበት እድል መፍጠር፣ የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ የመሳሰሉት ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም