በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን ለማስቆም ትውልዱን በእውቀት ማነፅ ይገባል - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

91

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 24/2014 (ኢዜአ) በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን በዘላቂነት ለማስቆም በእውቀት የታነፀ የትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

የአለም የሴቶች ቀን ማጠቃለያ መረሃ ግብር በባህርዳር ከተማ  በተካሄደበት ውቅት ፕሬዚዳንቷ  ለታዳሚዎች በቪዲዮ ኮንፍረንስ ባስተላለፉት መልዕክት "አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሟል" ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ከሀገሪቱ የእምነት፣ ባህልና ወግ ባፈነገጠ  መልኩ  ከህጻን እስከ መለኩሴ ያሉት ጭምር ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰዋል።

የተፈጸመውን ነውረኛ ድርጊትን እስከመጨረሻው ማስቆም የሚቻለው ትውልዱን  በትምህርት ቤት በሃይማኖትና በቤተሰበ ደረጃ ስለ ጾታዊ ጥቃት አስከፊነት በማስተማር  እንደሆነም አስታውቀዋል።

አዲሱን ትውልድ በእውቀት በማነፅና የአስተሳሰብ አድማሱን ከፍ በማድረግ ስነ ምግባር የተላበሰና ህግ የሚያከብር እንዲሆን መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ሴቶች በህልውና ትግሉ በግንባር ከመሰለፍ ጀምሮ በስንቅ ዝግጅት፣ ለተፈናቃዮች ሃብት በማሰባሰብና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ስራዎችን በተሳካ መፈጸም መቻላቸው ለቀጣይ ስራ ታላቅ ልምድ የተገኘበት እንደነበር ጠቅሰዋል።

ትውልድን ከቤት ጀምሮ ከማነጽ ባሻገር ሴቶች በመደራጀት በሀገራዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ  ግንባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዝዳንቷ አመልክተዋል።

ብቁና ተተኪ የሴት አመራሮችን  በተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠና  በማፍራት ለተጠቃሚነታቸውንና ለተሳትፏቸው  ማደግ ወሳኝ መሆኑን  ገልጸዋል።

ሴቶች በሀገሪቱ ለሚካሄደው ብሄራዊ ምክክር  ስራ መሳካት አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አሳስበበዋል።

በተለይም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ሴት ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት፣ ክህሎትና ስነ ምግባር ተላብሰው እንዲወጡ ማስቻል የሴት አመራሮች ሃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።

የዘንድሮው የአለም የሴቶች ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተሳታፊዎችም ወደ የአካባቢያቸው ሲመለሱም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በባህር ዳር ከተማ   በተካሄደው የአለም   የሴቶች ቀን መረሃ ግብር ላይ የአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተሞችን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም