ሕወሓት ለሰብአዊ ተኩስ አቁሙ እንዲገዛ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ መንግስት ጥሪ አቀረበ

87

መጋቢት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ማህረሰብ ሕወሓት ለሰብአዊ ተኩስ አቁሙ እንዲገዛ ግፊት ሊያደርግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የሰብአዊ ተኩስ አቁሙ የትግራይን ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኒታ ዌበርን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ ወቅታዊና ሰብአዊ እርዳታ ጉዳዮች እንዲሁም የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የጂኦፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አቶ ደመቀ በቅርቡ መንግስት ያሳለፈው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ውሳኔ የትግራይ ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቶችን ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

መንግስት ቃል በገባው መሰረት የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ከ22 በላይ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ሊገቡ መቃረባቸውን ተናግረዋል።

ሕወሓት ምክንያቶችን በመደርደር የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ የሚፈጥረውን ማስተጓጎል ማቆም አለበት፤ ለዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ ለተኩስ አቁሙ እንዲገዛ ተጽእኖ ማሳደር አለባቸው ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የወሰዳቸውን እርምጃ አስመልክቶ ለልዩ ልዑኳ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮችን በመፍታት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳትና ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ እየተደረገ ያለው ጥረት መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ያለውን ፍላጎት የሚያሳዩ ናቸው” ብለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኒታ ዌበር በበኩላቸው መንግስት በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁና ከሰብአዊ ተኩስ አቁሙ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች እንደሆኑ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

500 ሜትሪክ ቶን አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ዛሬ ትግራይ ክልል መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም