ወደ ቀያችን እንድንመለስ የሰብአዊ ድጋፍና የህግ ጥበቃ ሊደረግልን ይገባል-ተፈናቃዮች

64
ዲላ ነሀሴ 30/2010 ወደ ቀያቸው ተመልሰው የቀድሞ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ መንግስት የሚፈለገውን ድጋፍ እንዲያደርገላቸው ከምስራቅና ምእራብ ጉጂ ዞኖች ተፈናቅለው በጌዲዮ ዞን ገደብ ወረዳ የተጠለሉ ዜጎች ገለፁ ። አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሰጡ መካከል አቶ ፀጋዬ ሚጁ እንደገለፁት ከሚኖሩበት ምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ከነቤተሰቦቻቸው ተፈናቅለው ወደ ጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ በመምጣት በጊዜታዊ መጠለያ ሰፍረዋል ። "ተወልደን ያደግነው፣ ንብረትም ያፈራነው እዛው ቀርጫ ነው" ያሉት አቶ ፀጋዬ ይተዳደሩበት የነበረውን የግብርና ሥራ ትተው ባዶ እጃቸውን መውጣታቸውን ተናግረዋል ። መንግስት የምግብና የአልባሳት ድጋፍ እያደረገላቸው ቢሆንም ወደ ቀያቸው የመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት ያደረባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይሁንና ከተመለሱ በኋላ በቂ ድጋፍ ካላገኙና የፀጥታ ችግር ካጋጠማቸው ለሶስተኛ ጊዜ እፈናቀላለሁ የሚል ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል ። ወደ መጡበት ቀዬ ተመልሰው የቀድሞ ኑሯቸውን እንዲመሩ መንግስት በቂ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትና የህግ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው አቶ ጸጋየ ጠይቀዋል ። አቶ ልደቴ ጃርሶ በበኩላቸው ወደ ተፈናቀሉበት  ቀርጫ ወረዳ ቢሄዱም ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሰው ወደ ተጠለሉበት ገደብ ወረዳ መምጣታቸውን ገልፀዋል ። "በቂ የደህንነትና ጥበቃ ያለው በወረዳ ከተሞች ላይ ብቻ ነው" ያሉት አቶ ልደቴ ቀያቸው ገጠር አካባቢ በመሆኑ በፀጥታ ሥጋት ማሳቸውን ለማየት አለመታደላቸውን አብራርተዋል ፡፡ ወደ አካባቢያቸው የተመሱ ሰዎችም ምቹ ጊዜያዊ መጠለያና ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ መመልከታቸውን ጠቁመዋል። ተፈናቅለው ከቆዩበት ወደ አካባቢቢያቸው ከተመለሱ ዜጎች መካከል በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ኤጉ አባዪ ቀበሌ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ያገኘናቸው አቶ ጥላሁን በቀለ ወደ መጠለያው ከመጡ በኋላ ምንም አይነት ድጋፍ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል ፡፡ ያሉበት መጠለያ ምቹ አለመሆኑን የገለፁት አቶ ጥላሁን "ከዚህም በላይ የሚያሳስበን የፀጥታው ሁኔታ ነው" ብለዋል ፡፡ አቶ ጥላሁን እንዳሉት ማሳቸውን ለመጎብኘት ወደ ቀያቸው በሚሄዱበት ወቅት በተለያዩ ግለሰቦች ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው በመሆኑ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ብቻ ለመቆየት ተገደዋል ፡፡ "መጀመሪያም ችግሩን የፈጠሩት ጥቂት አጥፊ ግለሰቦች ናቸው" ያሉት አቶ ጥላሁን እንዲህ አይነት ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር ባለመዋላቸው በሥጋት ለመኖር መገደዳቸውን አስረድተዋል ፡፡ "አጥፊዎች በሕግ ተጠይቀው እንደበፊቱ በፍቅርና አንድነት መኖር እንፈልጋለን" ሲሉ ምኞታቸውን ገልፀዋል ። የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንደገለፁት በሁለቱ ሕዝቦች አባ ገዳዎች አማካይነት በተደረገ የዕርቅና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራ እንዲሁም በመንግስት በኩል በተከናወነ የፀጥታ ማስከበር ተፈናቃዮችን ለመመለስ አሰተማማኝ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል ። "ከተፈናቃዮች ጋርም መግባባት ተፈጥሯል" ያሉት አቶ ኃይለማርያም ጥፋተኞችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ ባለመጠናቀቁ ከሁለቱም ወገኖች ትንኮሳና አደናቃፊ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች እንደማይጠፉ ጠቁመዋል ። ሁለቱም ዞን አስተዳደሮች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ተንኳሽ ግለሰቦችን  ለሕግ የማቅረብ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እሰካሁን የቀረበው የአስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ከተመላሽ ተፈናቃዮች ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመገምገም እጥረቱን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ። ተፈናቅለው ወደ ጌዴኦ ዞን ከመጡ ዜጎች መካከል እስካሁን ከ359 ሺህ በላዮቹ ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ ቢሆንም 175ቱ ተመልሰው ወደ ዞኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል ። "ተፈናቃዮቹ ከመሬት ይዞታ ማረጋገጫ፣ በሰብአዊ ድጋፍ አለመሟላትና ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር በተያያዘ ተመልሰው መጥተዋል" ያሉት አቶ ኃይለማርያም ችግሩ እየተፈታ መሆኑን አስታውቀዋል ። የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት መከላከልና አፈታት አማካሪ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ደምሴ የአስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እጥረት መኖሩ በግምገማ ተረጋግጦ ማስተካከያ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ ትንኮሳ በመፍጠር ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ግለሰቦችን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ለህግ የማቅረብ ስራ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም