አምቦ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ 10 አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ሊጀምር ነው

100
አምቦ ነሀሴ 30/2010 አምቦ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ 10 አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ሊጀምር ነው። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሲስተር ሙሉ ኪታባ እንደገለጹት በትምህርት ዘመኑ ከሚጀመሩት መካከል ዘጠኙ የሁለተኛ ዲግሪ፤ አንዱ ደግሞ የሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ዲግሪ ከሚጀመሩት መካከል ፊዚክስ፣ ነሪሲንግ፣ ሃይዌር ምህንድስና፣ ኮንስትራክሽንና ቴክኖሎጂ ማናጅመንት፣ ምህንድስናና የስነ ልቦና የትምህርት ዘርፎች ይገኙበታል፡፡ በእንግሊዚኛ ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡ መርሃ ግብሮቹን ለመጀመር የሚያስችል የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ፣  የቤተ ሙከራ፣ የቤተ መፅሐፍት፣ የተማሪዎች ማደሪያና የመመገቢያ ቦታዎች ዝግጅት የተደረገ ሲሆን የመምህራን ቅጥርም እየተካሄደ ነው። እንደ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቷ ገለፃ ዩኒቨርስቲው በሚጀምራቸው አዳዲስ የስልጠና መርሃ ግብሮች ከ200 በላይ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ይጠበቃል። አዲስ የሚጀመሩትን ሳይጨምር ዩኒቨርሲቲው 58 የቅድመ ምረቃና 24 የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በመደበኛ፣ በማታውና በክረምት የትምህርት መርሀ ግብሮች በማከናወን ላይ ይገኛል ። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በ2011 የትምህረት ዘመን 5ሺህ 346 አዲስ ተማሪዎችን በመቀበል የቅበላ አቅሙን ወደ 25 ሺህ 500 ለማድረስ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም