በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሰው ሃይል ልማትና የቴክኖሎጂ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ ነው

78

 አዲስ አበባ  መጋቢት 22/2014 /ኢዜአ/ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሰው ሃይል ልማትና የቴክኖሎጂ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።

የኮርፖሬሽኑ  የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤትና የትራንስፎርሜሽን ክፍል ኃላፊ አዲሱ ማሞ በዚህን ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰለጠነ  የሰው ኃይል በማቅረብ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁ ባለሙያ ከማፍራት ባሻገር በቴክኖሎጂ ፈጠራ ፓርኮችን መደገፍ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም በአገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይ ከባህርዳር፣ አዳማና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀራርበው እየሰሩ ሲሆን በተወሰነ መልኩ ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጋር ትስስር መኖሩንም ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በፓርኮች እንዲሰለጥኑ እየተደረገ መሆኑንም  እንዲሁ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶክተር ሹሜ በርሄ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች  በንድፈ ሃሳብ የቀሰሙትን ትምህርት  በተግባር በመደገፍና ውጤታማ ስራ ለመስራት የሁለቱ ተቋማት ትስስር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች 85 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም