ኢንተርፕራይዞች ተገቢውን የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባ ተመለከተ

145

አዳማ፤ መጋቢት 22/2014(ኢዜአ) ኢንተርፕራይዞች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ተገቢውን የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባ ተመለከተ።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉና በተለይም በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ከ100 በላይ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበት የንግድ ትርዒትና ባዛር ዛሬ በአዳማ ከተማ ተከፍቷል።

የንግድ ትርዒትና ባዛሩን የከፈቱት  የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ባደረጉት ንግግር  ከውጭ የሚገባውን የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የምንችለው ኢንተርፕራይዞችን ማብቃትና ተከታታይ ድጋፍ ማድረግ ስንችል ነው ብልዋል።

ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት አልፎም ወደ ውጭ ለመላክ እንዲቻል የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ እንዲሪስ፤  የንግድ ትርዒትና ባዛሩ ኢንተርፕራይዞች ምርትና የፈጠራ ውጤታቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ለምርታቸው የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጭምር  እንደተዘጋጀም ተናግረዋል።

የግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማህበረሰብ በማቅረብና በገበያ ማረጋጋት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻልም እንዲሁ።

በተለይም በአምራች ዘርፉ የተሰማሩት የምርት ጥራትና ደረጃን በማሻሻል ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በቀጣይነትም በገበያ ትስስሩ በሀገር ውስጥና በውጭ  ገበያ የመወዳደር አቅም ለማጎልበት እንደሚሰራም የገለጹት ሃላፊው፤የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅቱ  እስከ 10 ሺህ ሰዎች እንደሚጎበኙ የመጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የንግድ ትርዒትና ባዛሩ የስራ ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ ሆነው ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የሚሸጡበት፤ በዚያውም ልምድ የሚቀስሙበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአዳማ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ናቸው።

በአዳማ ከተማ ለኢንተርፕራይዞቹ የብድር አቅርቦት፣ ተጨማሪ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎች ከማመቻቸት ባሻገር  ወደ መካከለኛ ባለሀብት እንዲሸጋገሩ ጭምር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

በዝግጅቱ ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ያቀረቡት የዝዋይ ዱግዳ የገዳ ማህበር ተወካይ ከድር ቦንሶ "በተሰማራንበት የግብርና ስራ ውጤታማ ሆነን በባዛሩ ምርታችንን ይዘን ቀርበናል" ብለዋል።

ከቀረቡት ምርት ውስጥ አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ25 ብር እየሸጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዝግጅቱ የገበያ ትስስር ከመፍጠሩም ባለፈ የተሻለ ልምድ አግኝተን ጥራት ያለውን ምርት በማምረት በቀጣይ ይዘን ለመቅረብ ጭምር ያዘጋጀናል ነው ያሉት።

በአዳማ ከተማ መስቀል አደባባይ በተከፈተው የንግድ ትርዒትና ባዛር ላይ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች የቀረቡበት ዝግጅት ለቀጣይ አምስት ቀናት ይቆያል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም