የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገሪቱ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት የሚያደርጉት ጥረት ውጤት እያመጣ ነው---የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ

87

ሶዶ መጋቢት 22/2014 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገሪቱ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት እያደረጉ ያለው ጥረት ግጭትን በመከላከል ውጤት እያመጣ ነው ሲሉ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አቶ አክሊሉ ለማ አስታወቁ።

የወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሃይማኖታዊ እሴቶች ለሀገር ሰላም ባለቸው ፋይዳ ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገሪቱ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት እያደረጉ ያለው  ጥረት ግጭትን በመከላከል በኩል ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የሁሉም ሃይማኖታዊ ተቋማት መመሪያ ሰላም በመሆኑ አስተምህሮታቸው "ለሀገር ሰላምና ፍቅር ያለው ትውልድ በመቅረጽ በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው " ብለዋል ።

"የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ድርጊት ለሙስና በር ከፋች በመሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ምእመናን የጽንፈኝነት  አስተሳሰብን ማውገዝና ማስወገድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።

የዞኑ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ አቶ ሚልክያስ ኦሎሎ በበኩላቸው ጉባኤው በየመዋቅሩ የሃይማኖታዊ እሴቶች ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት መጎልበት ሚና እንዲያበረክቱ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 "ጉባኤው በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ የሰላም ግንባታን በማጠናከር ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው" ብለዋል።

በሃይማኖት ሽፋን የሚንጸባረቁ የጥላቻ ንግግሮችና አስተሳሰቦች ለሰላም መደፍረስ ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ብርሃኑ ተድላ ናቸው።

አቶ ብርሃኑ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶችን በሃይማኖታዊ አስተምህሮና በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የሁሉም የእምነቶች መርሆች ፍቅር፣ ሰላም፣ መቻቻል፣ ፍትሃዊነት፣ ሰብአዊነትና መሰል የመልካም ስብዕና መገለጫ መሆናቸውን በመግለጽ "መርሆዎቹን ለሀገር ሰላምና መረጋጋት መጠቀም ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም