የቤንዚል እጥረት ስራችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል --- የደብረብርሃን አሽከርካሪዎች

147
ደብረብርሃን  ነሀሴ 30/2010 በየጊዜው እያጋጠማቸው ባለው የቤንዚል እጥረት የዕለት ተዕለት ስራቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን  በደብረ ብርሃን ከተማ  አሽከርካሪዎች ገለጹ። በከተማው ባለ ሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪዎች መካከል ወጣት ግሩም ብዙነህ ለኢዜአ እንዳለው   በቤንዚል እጥረት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት ለህብረተሰቡ  በመስጠት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያጣ ነው፡፡ ቤንዚን ይገኛል በተባለበት የነዳጅ ማደያ  ተራ በመያዝ ቀኑን ሙሉ ቢሰለፍም ሳይደርሰው ስራ በመፍታት መቸገሩን ፡፡ " የምሰራበት ባጃጅ የሌላ ሰው በመሆኑ በገባሁት ውል መሰረት በየቀኑ 100 ብር ለባለሃብቱ ገቢ ማድረግ ስላለብኝ በባንክ ቀደም ሲል ከቆጠብኩት እያወጣሁ ለመክፈል ተገድጃለሁ”ብሏል ወጣት ግሩም ፡፡ ሌላዉ ወጣት ተስፋሁን አወቀ በበኩሉ የቤንዝን እጥረት በየጊዜው የሚከሰት ችግር በመሆኑ በስራቸውን ላይ ተጽዕኖ አስድሮብናል ብሏል፡፡ ከጥቁር ገበያ ሊትሩን ቤንዚን እስከ 40 ብር በመግዛት መስራት ቢሞክሩም ከከተማው የታክሲ ትራንስፖርት  ታሪፍ አንጻር አዋጭ ባለመሆኑ ከነጓደኞቹ ተቸግረው እንዳሉ አመልክቷል። " ሁላችንም ከአንድ ማደያ ለመቅዳት ብንሰለፍም ማደያው ጧት ከአንድ ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ብቻ እንዲሰራ መደረጉ ቀኑን ሙሉ ስራ ፈትን ተሰልፈን ተራ ሳይደርሰን ለመሄድ እንገደዳለን "ብሏል፡፡ የኦይል ሊቪያ ቁጥር አንድ  ማደያ ተቆጣጣሪ አቶ ንጉሴ ፍልፍሉ ከሁለት ቀናት በፊት 26ሺህ ሊትር ቤንዚል ማስገባታቸውን ተናገረዋል፡፡ አቶ ንጉሴ  እንዳሉት በሌሎች ማደያዎች ቤንዚል የለም በማለት ሁሉም የባለ ሶስት እግር ታክሲ ባጃጆችና  ሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ወረፋ እየጠበቁ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ጥረት እያደረጉ ነው። አሁን ላይ የቀረ 18 ሺህ ሊትር ቤንዚል ስላለ  ተገልጋዮች ተረጋግተው በወረፋቸው ሊሰተናገዱ እንደሚገባ ጠቁመው ተጨማሪ ከጅቡቲ  ለማስመጣት መታዘዙን አመልክተዋል፡፡ "ይሁን እንጂ አንዳንድ  አሽከርካሪዎች ገና ያልቃል በሚል ስጋት ከቀዱ በኋላ በጀሪካ ገልብጠው  ተመልሰው  ስለሚሰለፉ ችግሩን አባብሶታል "ብለዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘይኑ አልይ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በከተማው ያሉ አምስት ማደያዎች ፈጥነው ቤንዚል እንዲያስገቡ  አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ ቤንዚን ማስመጣት እየቻሉ አለግባብ  ችላ በሚሉ ማደያዎች ላይ  እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ጠቁመዋል። " ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታትም ከኦይል ሊቪያ ቁጥር አንድ ያለውን ቤንዚል  አሽከርካሪዎችና ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም ባለሙያ ተመድቦ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ ነው” ብለዋል፡፡ የቤንዚል እጥረት በሚከሰትበት ወቅት ማደያዎች ሌሊት በህገ ወጥ ለነጋዴዎች እየሸጡ መሆኑ ተደርሶበት ሽያጩ ከጧቱ አንድ ሰዓት እሰከ ማታ 12 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲቀዳ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት አንድ ሺህ 375 ሊትር ቤንዚል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተገኝቶ መወረሱንና በዚህ ላይ ተሳትፎ በነበራቸው አራት ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጽህፈት ቤቱ አስታውሷል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም