ለውበት የተተከሉ ዛፎች በአስፓልት ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው

75
ሽሬ ነሀሴ 30/2010 በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ለውበት የተተከሉ ዛፎች በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ነዋሪች ገለፁ። ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ዛፎቹ እያደጉ በሄዱ ቁጥር ሰራቸው በከፍተኛ ወጭ የተገነባ የእግረኛ አስፓልት መንገድ በመሰነጣጠቅ እንዲፈርስ ምክንያት ሆኗል ። የደን ልማት ባለሙያና የከተማዋ ነዋሪ አቶ አንገሶም መረሳ በሰጡት አስተያየት ዛፎቹ በመንገድ ላይ ጉዳት እያደረሱ ያለው በጥናት ባለመተከላቸው ነው ። ከተሞች  ውስጥ የሚተከሉ ዛፎች  በጥናት የተተከሉ ባለመሆናቸው መንገዱን በመሰነጣጠቅ ችግር  ፈጣሪዎች ሆነዋል  ብለዋል፡፡ አቶ ቢንያም ታረቀ  በበኩላቸው በዛፎቹ ስር መሰንጠቅ የደረሰበት የአስፓልት መንገድ ለሰዎች እንቅሰቃሴ አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል ። እግረኞች በፈረሰ መንገድ ላይ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ለተሽከርካሪ በተከለለ አስፓልት መንገድ በመግባት ለአደጋ እየተጋለጡ መሆናቸውም ተጠቁማል። ዛፎቹ አሁን ላይ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘነ በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲፈልግ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል ። የከተማው ፅዳትና ውበት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ንጉሴ ገብረመድህን  ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው  በሰጡት ምላሽ ዛፎቹ ያለ ጥናት በህዝብ ተሳትፎ የተተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። የከተማው አስተዳደር ዛፎቹ በመንገድ ላይ እያደረሱ ያለውን ጉዳት በመረዳት ቀድሞ የተተከሉትን በማንሳት ውበት በሚጠብቁ ተስማሚ ዛፎች የመተካት ሰራ መጀመሩን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም