በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው አምስት የፍፃሜ ውድድሮች ተደረጉ

240

መጋቢት 21/2014/ኢዜአ/ በ51ኛዉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሶስተኛ ቀን ውሎው አምስት የፍፃሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በዛሬው ዕለት ፍጻሜቸውን ያገኙ ስፖርቶች የሴቶች ዲስከስና ምርኩዝ ከፍታ ዝላይ፣ በወንዶች ዲስከስ ውርወራ እና 110 ሜትር የወንዶችና የ100 ሜትር የሴቶች መሰናክል ሩጫ ፍፃሜ ተካሂዷል።

በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው የፍፃሜ ውድድሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ምርኩዝ ዝላይ ሁለት አትሌት ተካፋለዋል።

በዚህ የፍፃሜ ውድድር ከጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ የተወከሉት ሲፈን ሰለሞን 2 ነጥብ 10 ከፍታ በመዝለል አንደኛ ስትወጣ፤ ሜቲ ቤኩማ ደግሞ 2 ሜትር ከፍታ በመዝለል ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።

በወንዶች ዲስከስ ውርወራ ፍፃሜ ማሙሽ ታየ ከሲዳማ ቡና አንደኛ፣ ገበየሁ ገብረእየሱስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ፤ ኢብሳ ገመቹ ከአዳማ ከተማ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

በሴቶች ርዝመት ዝላይ ኪሩ ኢማን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ማሬዋ ፒዶ ከመከላከያ፤ አርያት ዴቪድ  ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል።

በወንዶች 110 ሜትር መሠናክል ማርሸት ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንደኛ፤ ኬሪዮን ሞርቴ   ከኦሮሚያ ክልል ሁለተኛ፤ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሮድቾል ከጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በ100 ሜትር መሠናክል ሴቶች ሂርጰ ዲርባና አለሚቱ አሰፋ ከኦሮሚያ ክልል አንደኛና ሁለተኛ፤ ምህረት አሻሞ ከመከላከያ ስፖርት ክለብ ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል ።

ከፍጻሜ ውድድሮች በተጨማሪ በ1ሺህ 500 ሜትር እና 200 ሜትር ሩጫ የማጣሪያ ውድድሮች ተደርገዋል።

የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።