‘ኤች.አር 6600’ ተገቢ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት የሚፈቅድ ነው

101

መጋቢት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ‘ኤች.አር 6600’ ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ ጣልቃገብነት ከመሆኑ ባለፈ በአገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ ይበልጥ የሚያባብስ መሆኑን የፖለቲካና የአስተዳደር ምሁር ገለጹ።

በአፍሪካ የጥናት ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪና በላይደን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ፖለቲካ እና አስተዳደር ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን አቢንክ እንደገለጹት ‘ኤች.አር 6600’ ተገቢ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት የሚፈቅድ ነው ሲሉ ኮንነውታል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ቀውስ አሜሪካ ወደ አንድ ወገን ያደላ በሚመስል መልኩ አቋም መያዟ ቀውሱን ለመፍታት ገንቢ ሚና እንዳይኖራት አድርጓታል ነው ያሉት።

አሜሪካ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ተገቢ ያልሆኑ ጣልቃ ገብነቶች ማካሄዷም ተገቢነት የለውም ሲሉ ነው በአሜሪካ ኮንሰርቫቲቭ ድረ-ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የኮነኑት።

በቅርቡ በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ውይይት ተደርጎበት ድምጽ እንደሚሰጥበት የሚጠበቀው ‘ኤች.አር 6600’ ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ከመፍጠር ይልቅ ሠላምን ያናጋል፤ ዴሞክራሲንም ያቀጭጫል ብለውታል።

ረቂቅ ሕጉ ኢትዮጵያ ከውጭ አገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍና ብድር እንዳታገኝ የሚወተውት በመሆኑ የኢትዮጵያ የመልማት መብት የሚጎዳ ግልጽ ጣልቃገብነት ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ጆን አውግዘውታል።

ሕጉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸማቸውን የጦር ወንጀሎች የማይገልጽና የአንድ ወገን አድሎአዊነት የሚንጸባረቅበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አድሎአዊ እና አቻ የለሽ ጣልቃገብነት የሚፈቅድ በመሆኑ ተገቢነት የለውም ብለዋል።

ረቂቅ ሕጉ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ የቆየ ወዳጅነትና የጋራ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን የባይደን አስተዳደር ሊገነዘበው ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም