በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም ላይ ውይይት ሊካሄድ ነው

60
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010 በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ውይይት ሊካሔድ መሆኑን የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አስታወቀ። ውይይቱ ከግንቦት 14 እስከ 17 ቀን 2010 በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንደሚካሄድ ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው። ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም የውይይት መድረኩን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ከ2008 ዓም ጀምሮ በነበሩት የሁለት ዓመት ተኩል የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ላይ ምክክር ለማካሔድ ዝግጅት ተጠናቋል። በመድረኩ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመት ተኩል አተገባበር በአገሪቱ በተከናወኑና በቀሪ ጊዜያት መከናወን በሚገባቸው ተግባራት ላይ ይመክራል ነው ያሉት። በዚህ መሰረትም ውይይቱ የሴቶችና ወጣቶች፣ የአርሶና አርብቶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍና የሲቪል ማሕበረሰብ ተብለው በተከፋፈሉ ክላስተሮች አማካኝነት እንደሚካሔድ ነው የገለጹት። በክልልና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሔዱት ውይይቶች ሲጠናቀቁም አፈፃፀሙ በፌዴራል ደረጃ ተገምግሞ በቀጣይ መካሔድ ስላለባቸው ተግባራት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አስረድተዋል። በምክክር መድረኩ ከባለድርሻ አካላትና ተሳታፊዎች የሚነሱ ዋና ዋና ሃሳቦች ላይ ውይይት በማድረግም የተገኙትን መልካም ተሞክሮዎች በማጠናከር ቀሪ ስራዎች የሚካካሱበት መንገድ ላይ ውይይት ይደረጋል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም