በአማራ ክልል ለቀጣዩ የመኸር እርሻ የሚውል ከ212 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለቀጣዩ የመኸር እርሻ የሚውል ከ212 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ተዘጋጀ

ደሴ፤ መጋቢት 19/2014 (ኢዜአ) ለቀጣዩ የመኸር እርሻ ለማዘጋጀት ከታቀደው ምርጥ ዘር ውስጥ እስካሁን በተለያየ የሰብል ዓይነት ከ212 ሺህ ኩንታል በላይ መሰናዳቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ ።
በክልሉ እያጋጠመ ያለውን የዘር እጥረትና የጥራት ችግር ማቃለል በሚቻልበት ላይ ዛሬ በደሴ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው፤ በቀጣይ የመኸር እርሻ ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል።
ከዚህም ከ140 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መሆኑን አመልክተው፤ እቅዱ እንዲሳካ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የግብዓት አቅርቦት ችግሩን ለማቃለል እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በተለይ የዘር እጥረትና ጥራት ችግር አርሶ አደሩ በልፋቱ ልክ ምርት እንዳያገኝ እያደረገ ነው።
ችግሩን ለማቃለል ለቀጣይ የመኸር እርሻ የሚሆን ከ246 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን በተደረገው ርብርብ ከ212 ሺህ ኩንታል በላይ መሰናዳቱን አስታውቀዋል።
የበቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ማሽላና ጤፍ ከተሰናዳው ምርጥ የሰብል ዘር ይገኝበታል፡፡
ባለፈው ዓመት ከ140 ሺህ ኩንታል ዘር ለአርሶ አደሩ መቅረቡን ያስታወሱት ምክትል ኃላፊው፤ ዘንድሮ አስቀድሞ በተደረገ ጥረት ያልተቀላቀለ፣ ምርታማና ፈጥኖ የሚደርስ ዘር እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ የግብርና ጥራት ደህንነት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስካሄጅ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እንዳሉት፤ ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተሰራ ነው።
"በክልሉ ባሉ 511 ዘር አቅራቢዎች እና 229 ዘር አምራቾች በኩል ያልተቀላቀለ፣ ምርታማ፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘር እንዲደርስ ባለስልጣኑ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ነው" ሲሉም አክለዋል።
የዘር አቅርቦት በአግባቡ እንዲከናወን ከማድረግ ጎን ለጎን ጥራቱ ያልተረጋገጠ ዘር በህገ ወጥ መንገድ ለማቅረብ የሚሞክሩ ህገ ወጥ ዘር አቅራቢዎችን በመከታተል የተገኙት ለህግ እየቀረቡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
"በቅርቡ በህገ ወጥ መንገድ ጥራቱና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ ዘር ለአርሶ አደሩ ሲያሰራጩ የተገኙ ተጠርጣዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ይገኛል" ብለዋል።
ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ በዘር አቅራቢዎችና አምራቾች ላይ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የደሴ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኔ ገብሬ ናቸው።
በምርጥ ዘር የለማ የሰብል መሬት በአርም እንዳይወረስ፣ ቅልቅል እንዳይኖረው፣ ባዕድ ነገር እንዳይገባበትና ውጤታማ እንዲሆን ደህንነቱ በመስክና በቤተሙከራ ይረጋገጣል" ብለዋል።