ለአካባቢያዊና አገራዊ ልማት መጠናከር በተደራጀ መንገድ እንደሚታገሉ የወላይታ ወጣቶች ገለፁ

70
ሶዶ ነሀሴ 29/2010 የዶክተር አቢይ አህመድን የመደመር መርህን በመደገፍ ለአካባቢያዊና አገራዊ ልማት መጠናከር በተደራጀ መንገድ እንደሚታገሉ የወላይታ ወጣቶች አስታወቁ፡፡ ''የወላይታ ወጣቶችን ንቅናቄ በምንና እንዴት መምራት ይቻላል'' በሚል ርእስ በሶዶ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡ የወጣቶች ተጠሪ ወጣት ተሰማ ባልቻ በዚሁ ጊዜ እንደገለፀው የአካባቢው ተወላጅ ወጣቶች ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ባህላቸውን ጠብቀው የአካባቢውን የልማት እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ ''አሁን በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ደግሞ የሚጠበቅብንን እንድንወጣ የበለጠ መነቃቃት ፈጥሮልናል''ብሏል፡፡ በመሆኑም ለአካባቢያቸው ልማትና ለአገር እድገት የበኩላቸውን ለመወጣት ወጣቶቹ በተደራጀ መንገድ ለመታገል መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም  አደረጃጀታቸውን በመጠቀም ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር ያለውን መቀራረብ የበለጠ ለማጠናከር ጠንካራ አሰራር እንደሚዘረጉ ተናግሯል፡፡ ''በተለይም በሲዳማና ወላይታ ህዝብ ላይ በግለሰቦች አነሳሽነት የተፈጠረውንና ሊቀጥል የማይገባውን የጠብ ድልድይ ለመስበር በትኩረት እንሰራለን'' ብሏል፡፡ ወጣት በረከት በቀለ በበኩሉ አሁን የተፈጠረውን አሰራር በግልጽ ለመደገፍና የተለያየ ሃሳብ ለማስተናገድ የሚችል እንዲሆን የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ የህብረተሰቡ ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በተገቢው ሁኔታ እንዲከበር፣ ፍትህ እንዲሰፍንና ሙስናን ለመቃወም በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን የገለፀው ደግሞ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጣው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት አሸናፊ ከበደ ነው፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የወላይታ ሶዶ መሰናዶ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር ጳውሎስ ባልቻ በበኩላቸው ህብረተሰቡን ከድህነት ለማላቀቅ የተማረና ወጣቱን ክፍል በነጻነት አደራጅቶ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ረገድ የወላይታ ወጣቶች በተደራጀ መንገድ የጀመሩት እንቅስቃሴ ለአካባቢው ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወላይታ ወጣቶች ንቅናቄ ''በምንና እንዴት መምራት ይቻላል'' በሚል በሶዶ ከተማ ትናንት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም