ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

638

መጋቢት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ጋር ከዶሃ ፎረም ጎን ለጎን ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ሁለቱም መሪዎች በሁለትዮሽ ግንኙነት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ሃሳብ የተለዋወጡ ሲሆን በቀጣይ የሁለቱን ሃገራት ትብብር እና ወዳጅነት በሚያጠናክሩ ነጥቦች ዙሪያ መክረዋል።

በተመሳሳይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኳታር ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ካሊፋ ጃሲም አል-ኩዋሪ ጋር መክረዋል።

የኳታር ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች የሚያደርገውን ድጋፍ ያደነቁት አቶ ደመቀ፤ የሁለቱን ሃገራት የህዝብ ለህዝብ አጋርነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል ።

የኳታር ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ ከማህበረ-ኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ በሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉ የሁለቱን ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው እምነታቸውን መግለጻቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።