በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የሕጻናት ፓርላማ በነገው ዕለት ይመሰረታል

105

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የሕጻናት ፓርላማ በነገው ዕለት እንደሚመሰረት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ነገ የሚመሰረተው የሕጻናት ፓርላማ አወቃቀሩ አገር አቀፍ ሲሆን 132 አባላት አሉት ተብሏል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ሕጻናት ፓርላማ እንዲኖራቸው ለበርካታ ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል።

ይሁንና እስካሁን ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ሁሉን አቀፍ አለመሆኑን ጠቁመው፤ በነገው ዕለት የሚመሰረተው ፓርላማ በአንጻሩ አካታች ነው ብለዋል።

ፓርላማው በዋናነት ሕጻናት ስለመብታቸው ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግና በሂደትም መብታቸውን የሚያስከብሩበት ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በሕገ-መንግሥቱ የተደነገጉትን መብቶች ሳይሸራረፍ ለማስከበር መሆኑን በመጠቆም።

ጎን ለጎንም ሕጻናት መብታቸውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን እድሜያቸው ሲደረስም የሕጻናትን መብት ዋነኛ ተቋርቋሪና አስከባሪ ለማድረግም ነው።

ፓርላማው ሕጻናት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ከወዲሁ ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉና የአገሪቱን የመንግሥት አሰራር እንዲያውቁ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ይህም ሕፃናት በመልካም ስብዕና እንዲያድጉና አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድም ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል።

የሕጻናት ፓርላማ የታለመለትን ግብ እንዲመታና በሂደትም ጠንካራ አደረጃጀት እንዲፈጥር የሁሉም አካላት ተሳትፎና ድጋፍ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ስለዚህም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣አጋር አካላት እንደሁም ኅብረተሰቡ ለፓርላማው መጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም