የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ዋጋ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ ተጠየቀ

2483

አዲስ አበባ  ነሀሴ 29/2010 የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ዋጋ መናር አሁን ካለው የገበያ ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ማስተካከያ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

ድርጅቱ በበኩሉ የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ድርጅቱ በ2010 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸምና በ2011 እቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ዛሬ አካሂዷል።

በዚህም ድርጅቱ የህትመት ዋጋ ላይ ያለውን ሁኔታ በማጥናትና በመፈተሽ የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በውይይት መድረኩ የተሳተፉት ዶክተር ታደለ ገድሌ የህትመት ዋጋ እጅግ የናረ እንደሆነ በመግለጽ ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

”ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለህትመት ዋጋ ተመን አሰጣጥ ላይ የህብረተሰቡን አቅም ባማከለ መልኩ ማስተካከያ በማድረግ ዋጋ ሊቀንስ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት” ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማህበር የመጡት አቶ ጌትነት አባተ በበኩላቸው የህትመት ዋጋ መናር በተለይ ለአንባብያን ችግር በመሆኑ ድርጅቱ ችግሩን ለመፍታት ከአገር ውስጥ ወረቀት አምራቾች ጋር በመተሳሰር መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

“የህትመት ዋጋው መናር ለአሳታሚዎችም ሆነ ተጠቃሚዎች አሁን ካለው የህዝቡ ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ አንፃር ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ በመሆኑ ድርጅቱ በዚህ ላይ አጽንኦት ሰጥቶ ማስተካከያ ሊያደርግ ይገባል” ያሉት ደግሞ አቶ ገብረክርስቶስ ሃይለስላሴ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ናቸው።

ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመጡት አቶ አዳነ በላይ እንዳሉት፤ ድርጅቱ የተገልጋዩን ፍላጎት በማሟላት በተለይም ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎች በአግባቡ መመለስ አለበት።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተካ አባዲ እንደገለጹት፤ ለህትመት ግብዓትነት ከውጭ የሚመጣው ወረቀት ዋጋ ከፍተኛ ነው።

ችግሩን ለመቅረፍ ድርጅቱ ከውጪ አገር የሚገቡ ግብአቶችን ለመተካት በአገር ውስጥ ከሚገኙ አምራቾች ጋር የተጠናከረ ትስስር በመፍጠር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል

በዚህም ከህትመት ዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ከገበያው ውድድርና ከስራ አቅርቦት ጋር ያለውን ሁኔታ በማጣጣም የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ ከድርጅቱ ጋር የሚጣመርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኮሚቴ ተዋቅሮ የጥናት ሰነድ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር እንደቀረበ ተጠቁሟል።

ጥራት ያለው ወረቀት እንዲያመርቱም ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ተካ ተናግረዋል።