በክልሉ ከ58 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለትና ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ወጪ በሂሳብ ምርመራ ተገኘ

84

ጋምቤላ፣   መጋቢት 17/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በተካሄደ የሂሳብ ምርመራ ከ58 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሰነድ ክምችት ፣የጥሬ ገንዘብ ጉድለትና ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ወጪ ማግኘቱን የክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አስታወቀ።

የመስሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር አቶ ኡሞድ ኦቹዶ በቅርቡ ለተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት፤ ግኝቱ  በ33 የክልልና የወረዳ መስሪያ ቤቶች ላይ በተካሄደ የሂሳብ ምርመራ  ነው።

ከግኝቶች መካከል ከ34 ሚሊዮን 208 ሺህ ብር በላይ የተሰብሳቢ ሰነድ ክምችት እና ከ432 ሺህ ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከ4 ሚሊዮን 297 ሺህ ብር በላይ የጡረታ፣ የልማትና ሌሎች መዋጮዎች ለሚመለከተው ተቋማት ፈሰስ ሳይደረጉ መገኘታቸውን ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል።

አቶ ኡሞድ እንዳሉት፤  ከ3 ሚሊዮን 672 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ተቆርጦ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ሳይደረግ የተገኘ ሲሆን፣ ከ9 ሚሊዮን 741ሺህ ብር በላይ ደግሞ ደረሰኝ ሳይቆረጥለት ወጪ ተደርጓል።

በተጨማሪም የመንግስትን የግዥና የጨረታ ደንብና መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ መገኘቱንና ሌሎችንም ክፍተቶች አብራርተዋል።

"ከሠራተኞች ከተከፋይ ሒሳብ፣ ለጡረታ እና ለልማት ተቆርጦ ፈሰስ ባላደረጉ ተቋማት ላይ ከክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮና ከገቢዎች ቢሮ ጋር በመተባበር የእርምት እርምጃ ለማስወሰድ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ዋና ኦዲት መስሪያ ቤቱ በመንግስት ተቋማት የሚታየውን የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ለማሻሻል ከመስሪያ ቤቶች ጋር በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጡንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ከፋይናንስ ኦዲት በተጨማሪ በተወሰኑ መስሪያ ቤቶች የክዋኔ ኦዲት በመጀመር ተቋማት የተጣለባቸውን ግብ ስለማሳካታቸው ምርመራ እንደሚካሄድም አቶ ኡሞድ አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፣ የኦዲት ግኝቱ መልካም አፈጻጸም ቢታይበትም ዋና ኦዲት መስሪያ ቤቱ ግኝት ላይ ብቻ ሳይሆን የባከኑ የህዝብና የመንግስት ሀብት በህግ አግባብ እንዲመለሱ ጭምር በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

ተቋሙ ከኦዲት ግኝቱ በተጨማሪ ሃብት በማስመለሱ ሂደትም የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በትኩረት እንዲሰራም አስገንዝበዋል።

የመስሪያ ቤቶች በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ላይ ያለባቸውን ጉድለት ለማረም በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ጥልቀት ያለው ምርመራ ማካሄድ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም