ለመልካም አስተዳደር መጓደልና ስራ አጥነት መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል- የሐረር ከተማ ነዋሪዎች

71
ሀረር ነሀሴ 29/2010 በሐረሪ ክልል ለሰላምና ጸጥታ ችግር  መንስዔ የሆኑ የመልካም አስተዳደር መጓደልና ስራ አጥነት መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ነዋሪዎች ጠየቁ። ነዋሪዎቹ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ከክልሉ አመራሮችና ፀጥታ አካላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በተወያዩበት ወቅት ነው ። በአገር ደረጃ የተደረጉ ለውጦች በክልሉ ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። ከተሳፊዎች መካከል አቶ ጌቱ ነጋሽ እንደተናገሩት የወረዳ አስተዳዳሪዎች በስራ ገበታ አለመገኘት ተገልጋዩን ለእንግልት እየዳረገ ነው ። "ክልሉን የሚያስተዳድሩ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ አመራሮች ቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት ነዋሪውን  ለምሬት ዳርጎታል" ብለዋል ። "በአገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ የማይደግፍ የክልሉ አመራሮች መኖራቸው ለጸጥታ ችግሮች አይነተኛ መንስዔ ሆነዋል" ሲሉም ተናግረዋል ። "በክልሉ ሰላምን በማስጠበቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰሩ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ በቄሮ ስም የሚነግዱ ወጣቶች እኩይ ተግባርን መከላከል ይገባል" ያሉት ደግሞ አቶ ኤልያስ መሀመድ ናቸው ። "በክልሉ የወጣቶች ስራ አጥነት መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል "ያሉት አቶ ኤልያስ በክልሉ የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ዱባለ አብዲ “ወጣቱ የጸጥታ ችግሮችን የሚፈጥሩ አካላትን ማጋለጥ እንጂ የመንግስት መዋቅር ተክቶ መስራት አይችልም” ብለዋል። ወጣቱ የልማትና የሰላም ሐይል በመሆኑ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገቢሳ ተስፋዬ በበኩላቸው በክልሉ የመልካም አስተዳደር መጓደልና የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ። ለግማሽ ቀን በተካሄደው ውይይት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም