መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ የማጓጓዝ ስራ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ይሰራል

105

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ የማጓጓዝ ስራ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ከሃምሌ 14 ቀን 2013 እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2014 ድረስ ወደ ትግራይ ክልል በአጋር አካላት አማካኝነት 51 ሺህ 497 ሜትሪክ ቶን ምግብና ቁሳቁሶች ለተረጂዎች መጓጓዙን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል በአፋር በኩል በየብስ ትራንስፖርት የላካቸው ሰብዓዊ እርዳታዎችና ነዳጅ በአሸባሪው ህወሓት እንቢተኝነት ምክንያት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ ድጋፎች ለትግራይ ክልል እንዲደርሱ መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጉን ገልጸው በአጋር አካላት በየብስ የሚጓጓዙ እርዳታዎች እንዲሳለጡ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአጋር አካላት አቅም እስከ ፈቀደ ድረስ በየቀኑ በረራዎችን እንዲያደርጉ መፈቀዱንም ገልጸዋል።

መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚደረገውን ሰብዓዊ ድጋፍ የማጓጓዝ ስራ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡

በአሸባሪው ህወሓት በኩል የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደርሱ ተመሳሳይ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባም ገልጸዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በማሰብ መንግስት ግጭት ማቆሙን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም