የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ፈረንሳይና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግስት የሰላም ውሳኔ መልካም እርምጃ መሆኑን ገለጹ

547

መጋቢት 17/2014 /ኢዜአ/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ፈረንሳይ እና አምንስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም  መወሰኑን መልካም እርምጃ መሆኑን ገለጹ።


የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቃል አቀባያቸው ስቴፋኒ ዱጃሪች በኩል ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡


የመንግስት ውሳኔ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆንም ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡


ለጋሾች እና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በትግራይ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ በእጥፍ እንዲያሳድጉም ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።


የፈረንሳይ መንግስት በበኩሉ በመግለጫው እንዳስታወቀው የመንግስትን እርምጃ እንደሚያደንቅ እና ውሳኔው በትግራይ ክልል ለሚገኙና ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያቀላጥፍ ገልጿል፡፡


የመንግስት ውሳኔ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቅሶ ሁሉም አካላት ሊቀበሉት እንደሚገባና አፈጻጸሙንም በቅርብ እንደሚከታተል አስታውቋል፡፡


ፈረንሳይ የልማት አጋሮቿን በማስተባበር ድጋፍ እንደምታሰባስብ እና በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ለጉዳት የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነችም ተገልጿል፡፡


በተመሳሳይም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ የመንግስትን ውሳኔ አዎንታዊ ሲል የገለጸው ሲሆን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በአማራ እና አፋር ክልሎችም ጭምር ለጉዳት ለተጋለጡ ሁሉ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡


የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን የመንግስትን ውሳኔ ሁሉም አካላት ሊያከብሩት እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል፡፡