ፈረንሳይ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን ትደግፋለች-አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ

82

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ፈረንሳይ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ አጋር የሆነችው ፈረንሳይ በጦርነቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ በተጨባጭ አጋርነቷን ማሳየቷን አውስተዋል።

አገራቸው ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመሆን በአማራ፣ በትግራይ፣ አፋር እና የደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ፕሮጀክቶችን እየተገበረች ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪ ፈረንሳይ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም አገራቸው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበትን የደሴ ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እየሰራች መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የፈረንሳይ መንግስት በፈረንጆቹ 2022 የመጀመሪያ ስድስት ወራት 10 ሚሊዮን ዩሮ ለመልሶ ማቋቋምና ምግብ ዋስትና ፕሮጀክቶች የሚውል ገንዘብ መድቦ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፈረንሳይ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማስፈን የወሰዳቸው እርምጃዎችን እንደምታደንቅም ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ወርሃ ሰኔ ላይ መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ ሲወስን ፈረንሳይ ውሳኔውን በጽኑ መደገፏን አስታውሰው፤ አሁንም አገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማ እንዲሆን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነች አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አይነተኛ ሚና እንዳላት የገለጹት አምባሳደሩ፤ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በአፍሪካ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

125 ዓመታትን ያስቆጠረውን የኢትዮ-ፈረንሳይ ወዳጅነት በመዘከር በቀጣይ በበርካታ ጉዳዮች በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

ሁለቱ አገሮች በታዳሽ ኃይል በተለይም ደግሞ ጂኦተርማል፣ ሎጂስቲክስና በግብርናው መስክ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶች እንደሚተገበሩ ገልጸዋል፡፡

የፈረንሳይ ባለሙያዎች ቡድንን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ ተቋርጦ የነበረውን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት ዳግም ማስጀመር መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ቤተ-መንግስትን ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር በሚከናወነው ሥራ ላይ ፈረንሳይ ተሳታፊ መሆኗንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም