በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት በግንባታው ዘርፍ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

96

መጋቢት 17/2014 /ኢዜአ/በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት በግንባታው ዘርፍ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመበት ወቅት ሃብት ከመዝረፍም ባሻገር የህዝብ መገልገያ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችን አውድሟል።

ቡድኑ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ መንገዶች፣ የግንባታ ማሽነሪዎች ዘርፏል መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አሰፋ ሲሳይ ለኢዜአ እንዳሉት የግንባታ መሰረተ ልማትና መሳሪያዎች ለህዝብ አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆነው ወድመዋል ።

በግንባታው ዘርፍ የደረሰው ውድመት በዝርዝር መጠናቱን ገልጸው፤ የጥናቱ ውጤት በቅርቡ በፕላን ኮሚሽን አማካኝነት እንደሚገለጽ ጠቁመዋል፡፡

ከፌዴራል መንግስትና ከድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር ጉዳት የደረሰበትን የግንባታ ዘርፍ እንዲያገግም ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

ለአብነት በምስራቅ አማራ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት በስድስት ከተሞች አስራ ስምንት ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የውል ስምምነት መወሰዱን ገልጸዋል።

በፌደራል መንግስት የተያዙት የወልዲያ_ጋሸና የመንገድ ግንባታን ጨምሮ የወልድያና ደሴ ከተሞች የፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሯል ብለዋል።

አካባቢው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ የግንባታ ጥያቄዎችን በአንድ ጊዜ መመለስ አስቸጋሪ ቢሆንም በሂደት ግንባታዎችን የማሳለጥ ተግባር ይከናወናል ብለዋል።

የፌዴራሉ መንግስት በክልሉ የጀመራቸው ግንባታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ በጦርነት የተጎዱ ቦታዎችን መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ ለአካባቢዎቹ በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

የግንባታ ቁጥጥርን በማጠናከርና የግንባታ ዲዛይኖችን በፍጥነት በማጽደቅ በጦርነት የተጎዳውን አካባቢ እንደግፋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም