የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል

101

መጋቢት 16 ቀን 2014(ኢዜአ) 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት በሐዋሳ ስታዲየም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፤ ውድድሩ ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ሻምፒዮናዎች ትልቁ መሆኑን ገልጸዋል።

የውድድሩ ዓላማ ለአትሌቶች የሥልጠና ልምምዳቸውን አቋም የሚለኩበትና ተተኪ አትሌቶች ለማፍራት ነው ብለዋል።

በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች ደግሞ በዚህ ዓመት ሰኔ ወር በሞሪሽየስ በሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚካፈሉ ይሆናል ነው ያሉት።

ሻምፒዮናው ከአዲስ አበባ ውጭ የሚደረገው የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ላይ መሆኑን ተከትሎ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚህ ውድድር ታዋቂ የሆኑ አትሌቶች ጭምር እንደሚካፈሉበት የተናገሩት ደግሞ በፌዴሬሽኑ የተሳትፎ ውድድር ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ  አስፋው ዳኜ ናቸው።

በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች እንደየደረጃቸው የገንዝብ ሽልማት እንዲሚሰጥም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ፌዴሬሽኑ ለዚህ ውድድር  ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንም ተናግረዋል።

በዚህ ሻምፒዮና ከሰባት ክልሎች፣ ሁለት ከተማ አስተዳደር፣ 24 ክለቦችና ተቋማት የተውጣጡ 620 ወንድና 413 ሴት አትሌቶች ይካፈሉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም