ለኢትዮ-ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ቀጣይነት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የዛላአንበሳ ነዋሪዎች ገለፁ

120
መቀሌ ነሐሴ 29/2010 ለኢትዮ-­ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ቀጣይነት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የዛላአንበሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ። የሁለቱም ህዝቦች ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ የተጀመረው ጥረት ከዳር ለማድረስ የሚያስችል ህዝባዊ መድረክ በዛላአንበሳ ከተማ ሰሞኑን ተካሄዷል። መልአከሃይለ ታረቀ ጠዓመ በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በጉሎመኸዳ ወረዳ በአካባቢው ህዝብ ተወክለው ወደ ኤርትራ ምድር በመዝለቅ የትግራይ ህዝብ ለሰላም ያለውን ዝግጁነት ከገለፁት ሽማግሌዎች አንዱ ናቸው። በወቅቱ ከኤርትራ ወገን የተሰጣቸው መልስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንደሚደገፍና ምንም እንኳን ባልታወቀ ምክንያት ቢቀሩም የህዝብ ተወካዮች ያሉበት ቡድን ወደ ዛላአንበሳ እንደሚላክ ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በሁለቱም አገራት የተጀመረው ሰላማዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይም የሁለቱ ህዝቦች ወደ ቀደመው ግንኙነታቸው እንዲመለሱ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ ወይዘሮ ሓሊማ አሕመድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እኛንም ይመለከታል ብለው በትግራይ ሰሜን ምእራባዊ ዞን ከሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ከመጡት ኤርትራዊያን  መካከል አንዷ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ያለው ፍላጎት የኤርትራ ስደተኞች ተቀብሎ ማስተናገድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር አሁንም እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል። አቶ ታደሰ ደመወዝ የተባሉት የዛላአንበሳ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ከ20 ዓመታት በላይ ተለያይተው የቆዩት ሁለቱም ህዝቦች እጅግ እንደሚነፋፈቁና ሰላማቸው ዘላቂ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በአካባቢው የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዘላቂ እንዲሆን ለተጀመረው ጥረት ቀጣይነት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የገለፁት ደግሞ ከኢሮብ  ወረዳ የተወከሉት ወይዘሮ ንግስቲ ዮውሃንስ ናቸው፡፡ ለረዢም ዓመታት ከተለየናቸው ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አዲሱን ዓመትና የመስቀል በዓልን በጋራ እንድናሳልፍ ሽማግሌዎች የጀመሩትን ጥረት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም