የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አደነቁ

102

መጋቢት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አደነቁ።

አንቶኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አሜሪካ ውሳኔውን እንደምትቀበለውና በብርቱ እንደምትደግፈው ገልጸዋል።

ያልተገደበ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር በመተባበር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ባወጣው መግለጫ መንግስት ዓለም ዓቀፉ የለጋሾች ማህበረሰብ እያቀረበ ያለውን ድጋፍ እና እርዳታ በ”ከፍተኛ መጠን” እንዲጨምር ጥሪ አቅርቧል።

በመግለጫውም የመንግስት ጥረት እና ቁርጠኝነት የሰብዓዊ ሁኔታውን በማሻሻል ረገድ የሚኖረው ስኬት የሚረጋገጠው በሌላኛው ወገን የሚገኘው አካል በተመሳሳይ ለዚህ አላማ በሚኖረው ቁርጠኝነት ልክ መሆኑን መንግስት እንደሚያምን አመላክቷል።

ይህ በመንግስት በኩል የተላለፈው ውሳኔ አላማው የአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ በነጻነት ተጓጉዞ ለእርዳታ ፈላጊ ዜጎች ለመድረስ እንዲችል እንደሆነም በግልጽ አስቀምጧል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም