በአሸባሪው ህወሃት የተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

215

ባህር ዳር ፣ መጋቢት 15/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በከፈተው ጦርነት ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው ለተመለሱና ሳይፈናቀሉ ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር ለተዳረጉ ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ዛሬ ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በፈፀመው ወረራ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

ወረራውን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደነበር ጠቁመው ሳይፈናቀሉ ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር የተዳረጉ መኖራቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም አሸባሪ ቡድኑ በሰሜኑ ግንባር እያካሄደ ባለው ትንኮሳ በደባርቅ፣ በቆቦና በዋግ ህምራ በርካታ ሰዎች በአዲስ መልክ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ባለፉት ወራቶች ተፈናቅለው የነበሩ ከ1 ሚሊዮን 143 ሺህ በላይ ሰዎችን ወደቀያቸው በመመለስ ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስና የመልሶ ማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

“በተጨማሪም ሳይፈናቀሉ በቀያቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለቆዩ ከ9 ሚሊዮን ለሚበልጡ ወገኖችም ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ተችሏል” ብለዋል።

ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው ያልተመለሱና በአዲስ እየተፈናቀሉ የሚገኙ ወገኖችን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች  ተፈናቅለው በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ከ692 ሺህ በላይ ወገኖችም በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ዶክተር ይልቃል አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስት ወገኖቹ  ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና መልሰው መቋቋም እንዲችሉ  የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

“የክልሉ መንግስት ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ለመስራት የተጀመረውን ውይይትና የትብብር ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።

የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሰብአዊ ድጋፍን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የአቅርቦት ዕጥረት እያጋጠመ በመሆኑ የክልሉ ህዝብ የመደጋገፍ ባህሉን እንዲያጠናክር ዶክተር ይልቃል  ጥሪ አቅርበዋል።

የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ተግባርን በተደራጀ አግባብ ለማከናወን መስተዳደር ምክር ቤቱ ራሱን የቻለ የፈንድ ጽህፈት ቤት አቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን አስታውቀዋል።

በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችና ኢትዮጵያዊያን፣ የፌዴራል ተቋማትና የክልል መንግስታት በህልውና ዘመቻው ያሳዩትን አብሮነት በመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር ይልቃል እንዳሉት በህልውና ዘመቻው የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ ለመቀልበስ በተደረገ እንቅስቃሴ ከባለሃብቱ፣ ከንግዱ ማህብረሰብ፣ ከመንግስት ሠራተኛውና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በጥሬ ገንዘብ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

በዓይነትም ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ተሰብስቦ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል።

”የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በደምና በአጥንት፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በስነ-ልቦና የተሳሰሩ ናቸው” ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ናቸው።

ዛሬም የአማራ እና የትግራይ ህዝብ ይህንኑ ትስስራቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑን ጠቁመው፣ ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ ወንድም አማራ ህዝብ ለመጡ የትግራይ ተወላጆች ህዝቡ ፍቅር ሰጥቶ ያለውን በማካፈል እየተንከባከባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ነዋሪ  ለተፈናቃይ የትግራይ ወንድሞች እንክብካቤ በመስጠት ያሳየውን ወገናዊነት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል ።

 መላ ኢትዮጵያዊያን  በክልሉ በአሸባሪ ቡድኑ የደረሰውን ጉዳት ተገንዝበው የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ስራ ለማስጀመር እስካሁን ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

 አሸባሪው ህወሓት ካደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንጻር የመልሶ ማቋቋም ሥራው ሰፊ ሃብት የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ በቀረበው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሪፖርት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ሪፖርቱ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።