በትግራይ አዲስ የመምህራን ምዘና ስርአት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

101
አክሱም ነሀሴ 29/2010 በትግራይ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመማር ማስተማር ሂደትን መሰረት ያደረገ ውጤት ተኮር አሰራርን ለመተግበር መዘጋጀቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በአክሱም ከተማ ለሶስት ቀን የተካሄደ ክልል አቀፍ የትምህርት ኮንፈረንስ  ትላንት ተጠናቋል፡፡ የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ገብረመስቀል ካህሳይ እንደገለፁት በክልሉ የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ በ2011 የትምህርት ዘመን  የትምህርት አደረጃጀትና አሰራር በአዲስ መልክ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል። በተለይ የመማር ማስተማር ሂደት ማዕከል ያደረገ የመምህራን ውጤት ተኮር ምዘና አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል ። "አሰራሩ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽኖ እያደረሱ ያሉ  ችግሮችን በመፍታት መፍትሄ የሚሰጥ ነው"  ያሉት ሀላፊው መምህራን ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት በመስጠት ተማሪዎችን የማብቃት ስራ እንዲያከናውኑ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ "አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ የመምህራን አቅም ግንባታና የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው" ብለዋል ። የትምህርት ጥራትን ለማረጋጋጥ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ፓኬጆች ተቀርፀው ወደ ትግበራ መገባቱንም ለአብነት ጠቅሰዋል ። መንግስት ለሁሉም ዜጋ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡ የታሕታይ አዲያቦ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መምህር የማነ ብርሃን በወቅቱ እንደገለፁት እየተሰራበት የነበረው የመምህራን የምዘና ስርአት የትምህርት ጥራት ከማረጋገጥ ይልቅ አሉታዊ ጎኑ ያመዘነ ነበር ። "የምዘና ስርአቱ የመማር ማስተማር ሂደትን መሰረት ያላደረገና  የተማሪዎች ብቃትን  ያለገናዘበ ነበር" ያሉት ሀላፊው ሁሉንም ተማሪ ከክፍል ወደ ክፍል የማሳለፍ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ እንደነበር ጠቁመዋል ። በክልሉ የሚዘረጋው አዲስ የምዘና ስርአት አሰራርና መለኪያም ሁሉንም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ  መዘጋጀት እንዳለበት  ጠቁመዋል። በመቀሌ የሰሜን ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እየሱስ ገብረእግዛብሄር  በበኩላቸው የተማሪዎች ብቃት፣ ውጤትንና መማር ማስተማርን መሰረት ያደረገ የመምህራን መዘና ለትምህርት ጥራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል ። እንደ ምክትል ሀላፊዋ ገለፃ የምዘና ስርአቱ  በመምህራን ላይ  የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት፣ ብቁ ዜጋ ለማፍራትና ሙያዊ  ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ያደርጋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም