የዲላ ከተማ ነዋሪዎች መንግስት የዋጋ ንረትና የመሰረተ ልማት ችግሮችን እንዲፈታላቸው ጠየቁ

151

ዲላ፣ መጋቢት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን የዲላ ከተማ ነዋሪዎች መንግስት የዋጋ ንረትና የመሰረተ ልማት ችግሮችን እንዲፈታላቸው ጠየቁ።

በከተማዋ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ህዝባዊ የውይይት መድረከ ትናንት ተካሂዷል።

በመድረኩም ህዝቡ ከዋጋ ንረት፣ ከመሰረተ ልማት፣ ከመልካም አስተዳደር እንዲሁም ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከአደረጃጀት ጋር በተያያዘ አሉ ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተው ውይይት ተደርጓል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ውዴ በየነ መንግስት በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ከህዝብ ጋር በቅርበት መወያየቱ  ለለውጥ ቆርጦ መነሳቱን እንደሚያስይ ተናግረዋል።

በዲላ ከተማ በመሰረተ ልማት ስር የሰደደ ችግር መኖሩን  ጠቁመው፤ በተለይ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥና የንጽህ መጠጥ ውሃ እጥረትና የኑሮ ውድነት ነዋሪውን እያስመረሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"ስግብግብ ነጋዴዎች ምርት በመደበቅና በየዕለቱ ዋጋ በመጨመር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል እያሰቃዩ ይገኛሉ "ብለዋል።

መንግስት  የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ከድርጊታቸው ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ከዓመታት በፊት ዞኑን ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚያገናኙ "የዲላ- ቡሌ- ሀሮዋጩ" እና "የፍሳገነት-አማሮ-ቡርጅ" የአስፓልት መንገዶች ግንባታ በተገባው ቃል መሰረት ሳይጀመር በመቅረቱ  ህዝብን ለእንግልልትና ለቅሬታ መዳረጉን የተናገሩት ደግሞ አቶ ታሪኩ ታደሰ ናቸው።

በተለይ የፍሳገነት አማሮ ቡርጅ መንገድ አገልግሎት እንዳይሰጥ በሸኔ የሽብር ቡድን ከአንድ አመት በላይ በመዘጋቱን በዞኑ ላይ የደህንነት ስጋት የደቀነ መሆኑን በማስገንዘብ፤ ችግሩ እንዲፈታ ጠይቀዋል።

ህዝቡ ለአስተዳደር ጉዳዮች ጥያቄዎቹ በቅርበት ምላሽ ለማግኘትና ከደቡብ ክልል በስነ ምህዳር መነጠሉን ተከትሎ ላነሳው የአደረጃጀት ጥያቄ ትኩረት እንዲሰጠውም አመልክተዋል።

ወይዘሮ ቅድስት አስራት የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በከተማዋ መሰረተ ልማት በፍትሃዊነት ተደራሽ አለመሆኑ ነዋሪዎችን ለቅሬታ መዳረጉን ገልጸዋል።

"ከቅሬታ ባሻገር መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደህዝብ የሚጠበቅብንን ለመደግፍ ዝግጁ ነን" ሲሉም ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አውሉ አብዲ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ለመግባባትና የጋራ ዕቅድ ለማዘጋጀት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ከህዝብ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት መንግስት ሌት ተቀን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

ፓርቲው የህዝብን ሰላምና ደህንንት ከማስጠበቅ አልፎም ልማትና ብልጽግናን ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን በጉባኤው መወሰኑን አመልክተዋል።

ውሳኔው ያለህዘብ ተሳትፎ የሚሳካ ባለመሆኑ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በአገሪቱ ለተፈጠረው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የአሻጥረኛ ነጋዴዎች ሴራ የጎላ መሆኑን ያነሱት ደግሞ ሌላዋ የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ፍጹም አሰፋ ናቸው።

ምርት በመደበቅ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ለሚወሰደው እርምጃ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ "መንግስት ምርት በድጎማ የማቅረብና ህገወጦችን የመቆጣጠሩን ተግባር ያጠናክራል" ብለዋል።

የስራ አጥነት ችግር የሀገሪቱ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ፍጹም መንግስት የሚቀጥረው የሰው ሃይል ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋምና መደገፍ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ሰፊውን የሰው ሃይል የሥራ ባለቤት የሚያደርገው የግሉ ዘርፍ በመሆኑ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከተሞችና ነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩ አሳስበዋል፡፡ 

የአደረጃጀት ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ጉዳይ በመሆኑ በራሱ መንገድ እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም