የሴቶች ተደራጅተው በጋራ መንቀሳቀሳቸው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያግዛቸዋል- የሴቶች ፌዴሬሽን

360

ፍቼ መጋቢት 15 /2ዐ14/ (ኢዜአ) ሴቶች ተደራጅተው በጋራ መንቀሳቀሳቸው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥና በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነትን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስገነዘበ፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽንና የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት ዛሬ በፍቼ ከተማ መክረዋል።

ፀረ ሰላም ሃይሎች በሀገራችን ሴቶች ላይ የሚፈፅሙት ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት፣ ግድያና ማፈናቀል የሚወገዝና ሴቶች ሊታገሉት የሚገባ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

እለቱን በማስመልከትም በፀጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ሴቶች ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስና የ100 ሺህ ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ኘሬዝዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ በወቅቱ እንደገለፁት ሴቶች ተደራጅተው በጋራ መንቀሳቀቸው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን የላቀ ያደርገዋል፡፡

ከተበታተነ ሃይል የተሰባሰበ ሃይልና የተደራጀ አቅም የተሻለ ተደማጭነት እንደሚኖረው ያመለከቱት ፕሬዝዳንቷ፤ “ለዚህም ሴቶች በጋራ ተደራጅተው መረዳዳትና መንቀሳቀስን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል” ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት  በብዙ ፈተናዎችና ችግሮች እያለፈች መሆኑን ጠቁመው በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ እንደ ሸኔ ባሉ ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚፈፀም አስነዋሪ ድርጊት ሴቶች የአካልና የስነ-ልቦና ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ያወሱት ወይዘሮ አስካለ፤ “ይህን አስከፊ ተግባር ሁሉም አካላት በትብብርና በአንድነት ሊታገሉት ይገባል” ብለዋል ፡፡

ሌላው አስተያየት የሰጡት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ ወይዘሮ ፅጌ ታደለ “ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረን ትግል ለማስታወስ የሚከበር ነው” ብለዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ሴቶች በሀገሪቱ ያሉ ፈተናዎችን በብቃት ለማለፍና መልካም እድሎችን ለመጠቀም ሊታገሉ ይገባል ” ሲሉም አክለዋል፡፡

የኦሮሚያ ሴቶች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ኮማንደር ሽቶ ሊካሣ በበኩላቸው “ጥቃትን የመከላከልና ሴቶችን የማብቃት ተግባር ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው አይደለም” ብለዋል፡፡

ሁሉም ወገን የበኩሉን በማበርከት ሴቶችን ከጥቃትና ከአፍራሽ ተግባር ሊታደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ  የሰሜን ሸዋ ዞን የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ያሬድ ግርማ ፀረ-ሰላም ሃይል የሆነው ሸኔን በቁርጠኝነት መታገል ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ የሰላም ጥያቄ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሴቶችና ህፃናት በዚህ ግፈኛ ድርጅት የሚደርስባቸው ግፍና መፈናቀል በተባበረ የህብረተሰብ ትግልና ክንድ የሚቆምበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበአሉ ላይ ከፌደራልና ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ሴቶችና የስራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በልዩ ልዩ ምክንያት የተፈናቀሉ ሴቶች ተገኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽንና በኦሮሚያ ክልል ሴቶች ፌደሬሽን አስተባባሪነት ከተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ሴቶች ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስና የ100 ሺህ ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተበርክቷል፡፡