የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች የልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲፈታላቸው አመለከቱ

151

አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 15/2014 (ኢዜአ) መንግስት በልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈታላቸው በአርባ ምንጭ ከተማ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተወያዩ ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡

ከብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ርስቱ ይርዳውና ዶክተር ሊያ ታደሰ ጋር የተወያዩት  ነዋሪዎቹ ሊፈቱላቸው የሚፈልጓቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አንስተዋል ፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ድንቅአለም ጌታሁን፤ አርባ ምንጭ ከተማ ባላት የመልማት አቅም ልክ እንድታድግ የሚያግዙ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች አለመኖራቸውን ተናግረዋል ፡፡

በአካባቢው የሚመረተውን የፍራፍሬ ምርት የሚያቀነባብሩ የአግሮ ኢንዱስትሪ፣ የአባያና ጫሞ ሀይቆችን መሰረት ያደረጉ የባህር ትራንስፖርት እና ግብርናን ቴኬኖሎጂዎች  አለመኖራቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

በአካባቢው ለመገንባት ቃል የተገቡና ያልተፈጸሙ የመሰረተ ልማት ፈጥነው ወደ ተግባር መሸጋገር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው የህብረተሰብ ክፍል መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን ቤት ሰርቶም ሆነ ገዝቶ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም ያሉ ደግሞ አቶ ዘላለም አበባው ናቸው።

በተለይ የመሬት ሊዝ ሽያጭና በዘርፉ የሚስተዋለው ደላላ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል እየጎዳ በመሆኑ መፍትሄ ያስፈልገዋል ብለዋል ፡፡

የሴቶች እኩልነት መረጋገጥ እንዳለበት በአደባባይ ቢነገርም ጉዳዮቻችንን ለማስፈፀም ወደ ሃላፊዎች ስንቀርብ የሚገጥመን ተቃራኒው ነው የሚሉት ወይዘሮ ሽታዬ ዘካርያስ  የተባሉ ተሳታፊ ናቸው ፡፡

በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ጉዳዮች የሚፈፀሙት በቡድንተኝነትና ወገንተኝነት እንደሆነ የተናገሩት ወይዘሮ ሽታዬ፤ በተለይ የአርባ ምንጭ ማዘጋጃ ቤት አካባቢ አገልግሎቶች የሚፈጸሙት በደላሎች አማካይነት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በአካባቢው እስካሁን ትኩረት ያልተሰጠው የከተማ ግብርና ልማት ቢሰራበት ለአካባቢው የፍጆታ አትክልቶችን በማቅረብ  የኑሮ ውድነት  ለማቃለል እንደሚረዳም ጠቁመዋል።

በሕገወጥ ሰፋሪዎችና በአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ምክንያት ህልውናው ሥጋት ላይ የወደቀውን የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ጉዳይ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ ዘውዴ ከህዝቡ የተነሱ ሀሳቦች ተገቢነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ፤ሀሳቦችን  በዕቅድ ግብአትነት በመጠቀም ደረጃ በደረጃ ጥያቄዎቹን ለመመለስ  ይሰራል ብለዋል ፡፡

የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሌብነትና ከአድሏዊ አሰራር እንዲላቀቁ የተጀመሩ ሥራዎችንም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ፓርቲው ህዝብ የሰጠውን ይሁንታ ተቀብሎ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሻገር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለውጡን ባልወደዱና ሀገሪቱን ለማፈራረስ አቅደው በሚንቀሳቀሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ አውስተው፤ ይህንን በጥልቀት መረዳትና ለመሻገር ተጋግዞ መስራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል ፡፡

ሁሉም የሚፈልገውን እድገት ለማምጣት ሰላም ማረጋገጥና እኔ ብቻ ከሚል ፅንፈኛ አስተሳሰብ በመውጣት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት ፡፡

ለመንግስት የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ህዝብን የመፍትሔ አካል ማድረግና በየጊዜው ያሉበትን ደረጃ በጋራ እየገመገሙ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ  ዶክተር ሊያ ታደሰ ናቸው፡፡

መንግስት በሀገሪቱ የተጠያቂነት ሥርዓትን ለመዘርጋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ የህዝብ ድጋፍ በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

መንግስት በተለይ የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ለማስፋትና በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶክተር ሊያ ፤ግንባታው በመገባደድ ላይ የሚገኘውን የአርባ ምንጭ ሪፈራል ሆስፒታል በቶሎ ወደ ሥራ ለማስገባት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጥረት ይደረጋል ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም