በከተሞች የሚከናወኑ መሰረተ ልማቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ ድጋፍ እየተደረገ ነው

65

ጎንደር፤ መጋቢት 14/201 /ኢዜአ/ በከተሞች የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የከተማና መስረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ በጎንደር ከተማ በዓለም ባንክና በመንግስት በጀት እየተከናወኑ ያሉ መሰረተ ልማቶችን አፈጻጸም ትናንት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ማጠናቀቂያ ላይ ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ከፍተኛ በጀት የተመደበላቸው የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል  ክትትል እየተደረገ ነው።

በአንዳንድ ከተሞች በግንባታ መጓተትና መቋረጥ እንዲሁም በጥራት መጓደል የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ተከታትሎ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ የተጓተተውን የአዘዞ - መሰረት ትምህርት ቤት የ10 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ ችግሩን ፈትቶ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ከሥራ ተቋራጩና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ምክክር መደረጉንም አስረድተዋል።

መንገዱን የሚገነባው የራማ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር መብራቱ ሃይሉ በበኩላቸው፤ የመንገድ ግንባታ ስራው የፋይናንስና የሲሚንቶ እጥረት ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ችግሩ መፈታቱን ገልጸዋል።

እስከ ሰኔ ወር 2014 መጨረሻ የ6 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራውን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ  ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዓለም ባንክ በብድር በተገኘ የ500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በከተማው ከ100 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፕሮጀክቶቹ አስተባባሪ አቶ ታምራት ልኡልሰገድ ናቸው፡፡

እሳቸው እንዳሉት ፤ በከተማው 8 መካካለኛና ከፍተኛ ድልድዮች እንዲሁም  የ10 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍና  የ4 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ  እየተካሄደ  ነው።

በተጨማሪ የመናፈሻ፣ የፓርኮችና የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት ግንባታዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የከተማ አስተዳዳሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ፤ በከተማው የአስፓልትና የጠጠር መንገዶችን ጨምሮ በርካታ መሰረተ ልማቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ ፍጥነትና ጥራት እየተከናወኑ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተትና የጥራት ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከአዘዞ እስከ  መሰረት ትምህርት ቤት ያለው የአስፓልት መንገድ ግንባታን የካሳ ክፍያ በማጠናቀቅ ከሦስተኛ ወገን ነጻ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሰረተ ልማት ጉብኝቱ ላይ የከተማ አስተዳዳሩ ከፍተኛ አመራሮችና የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የሥራ ተቋራጮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም