በአገር የማዳንና የህልውና ዘመቻው ወቅት የጤና ባለሙያዎች ያበረከቱት ሙያዊ አስተዋጽኦ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ነው

መጋቢት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገር የማዳንና የህልውና ዘመቻው ወቅት የጤና ባለሙያዎች ያበረከቱት ሙያዊ አስተዋጽኦ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የጤና ዋና መምሪያ በህግ ማስከበር፣ በህልውና እና በዘመቻ ህብረብሔራዊ አንድነት ወቅት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሰራዊት አባላትና ሲቪል ሰራተኞች ሽልማትና እውቅና ሰጠቷል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልእክት በአገር የማዳንና የህልውና ዘመቻው ወቅት የጤና ባለሙያዎች ያበረከቱት ሙያዊ አስተዋጽኦ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር መሆኑን ገልጸዋል።

ከጤና ሚኒስቴር፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎች ጋር በመቀናጀት በዘመቻው ወቅት የተሻለ የጤና አገልግሎት መሰጠቱንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል።

ለዚህም ተቋማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ የመከላከያ ሆስፒታሎችን ለማብዛት፣ ጠንካራ የጤና አገልግሎት ሰራዊቱ እንዲኖረውና የጤና ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የመከላከያ የጤና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ፤ ሰራዊቱ ተልዕኮውን በሚፈለገው መንገድ እንዲወጣ ድጋፍ ሰጪዎች የራሳቸውን የላቀ ሚና መወጣታቸውን ገልጸዋል።

ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር ዋና መምሪያው ለሰራዊቱ ከፍተኛ አገልግሎት መስጠቱንም ገልፀዋል።

ዘመናዊ የጤና አገልግሎት በብቃት ለመስጠት የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው በጤና መምሪያው ስር የሚገኙ የጤና ተቋማት በቁሳቁስ እና በሰው ኃይል የማጠናከር ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

የማዕረግና የዕድገትና እውቅና ካገኙት የተቋሙ ሰራተኞች መካከል

ኮሎኔል ሽብሬ ማሚቴ ና ዶክተር ሲሳይ ኤርገቡስ   የተሰጣቸው እውቅና ለበለጠ ስራ እንደሚያነሳሳቸውም ተናግረዋል።

በመረሃ-ግብሩ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች እንዲሁም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም